ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ የልደት በዓልን አስመልክቶ ቃለ ቡራኬ አስተላለፉ

«ኦ ትሕትና ዘመጠንዝ ትሕትና?» ወይ ትሕትና ዋ ትሕትና እንደምን ያለ ትሕትና ነው? «ኦ አፍቅሮተ ሰብእ ዘመጠንዝ አፍቅሮተ ሰብእ» ወይ ሰው መውደድ ዋ ሰው መውደድ እንደምን ያለ ሰው መውደድ ነው? በዚች የሰው ፍቅር አምላክ ሰው ሆነ ሰውም አምላክ ሆነ፣ ከድንግል ተወለደ፣ በጨርቅ ተጠቀለለ፣ በበረት ተኛ። ኦ ትሕትና ያለው አሁን ይተረጎማል፦ ለልማዲዱ ሕጻናት ሲወለዱ አናት እንዳይወርዳቸው፣ አካል እንዳይዛባባቸው ዘውረ ዓይን እንዳይገጥማቸው በጥንቃቄ ታቅፈው ይይዟቸዋል እንጂ ወዲያውኑ አያስተኟቸውም። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ወዲያውኑ እንደተወለደ በግርግም ተኛ መንክር ወመድምም ወእፁብ ግብር (ግሩም መድምም ዕፁብ ድንቅ ሥራ ነው)። ጌታ አገልጋይ ሆነ ሰውም ተገልጋይ ሆነ። ጌታ ሕጻን ኢየሱስ ክርስቶስ በጎል ተጣለ በጨርቅ ተጠቀለለ ቡቱቶ ለበሰ ብርዱን ቁሩን ታገሠ። ይኸውም ፍፁም አምላክ ፍፁም ሰው ተብሎ ነው።  የቴስቢያዊው ነብዮ ኢልያስ ሲወለድ በእሳት ስፋድል ተጠቅልሎ ነው። ዜና ድርሳነ ኤልያስ እንደሚያስረዳው በዚህም እናት አባቱ ፈሩ ደነገጡ ይላል። ጌታችን መድኃኒታችን ሲወለድ ግን ያለበሱት ጨርቅ ነው። ቅዱስ ያሬድ «እናቱ ቡርክት ማርያም በበለስ ቅጠል ጠቀለለችው አለበሰችው» ይላል። ይኸውም በእፀበለስ ምክንያት የወደቁትን አዳምን እና ሔዋንን የካሰላቸው ካሣ የከፈለላቸው መሆኑን ያጠይቃል። የኤልያስ ወላጆች እንደደነገጡ ቡርክት ማርያም አልደነገጠችም። እንዲሁም አረጋዊው ዮሴፍም አልፈራም ረዳቷ ሰሎሜም አልተሸበረችም። ጌታ በጎል መወለዱን የሚያመለክት ከአዳም ሰባተኛ በሆነው በሔኖክ መጽሐፍ ላይም ተጽፏል። «ወአስከብዎ ለውእቱ ሰይፍ» ያንን ስለት ያንን ኃያል ሰይፍ በበረት አስተኙት ተብሏል። መንክር ወመድምም የዳዊት ጋሻ በቤተልሔም ዋሻ ነቢየ እግዚእ ዳዊት «አቤቱ ጋሻዬ ሆይ ጠላቶቼን በኃይል በትናቸው» ብሎ የተናገረለት መድኃኒት ክርስቶስ በቤተልሔም ተወለደ። ቤተልሔም የሰላም የፍቅር የበጎ ነገር ምሳሌ ቦታ ናት። የሰላም የሕግ መንቂያ መፍለቂያ ቦታ ናት የሰላም ወንጌልም በእርሷ ተገኝቷል። ኦሪት የተገኘችባት ደብረ ሲና ተራራ ግን በጉምና በጢስ በእሳት በነፋስ በጭጋግ በድምጸ ነጋሪት ተከብባ ተጨንቃ በመራድና በመንቀጥቀጥ በፍርሃትና በመደንገጥ ነበረ። መምህረ ኦሪት ሙሴም ይህንን ሁሉ ተመልክቶ የሚከተለውን ተናገረ፦ ርዑድ ወድንጉፅ አነ - እኔ የምፈራ የምደነግጥ የምርድ የምንቀጠቀጥ ሰው ነበርኩኝ አለ። የቤተልሔሙ ሰው አረጋዊው ዮሴፍ ግን ሰላም፣ አድናቆትና መረጋጋት ሰፍነውበት ይታይ ነበር።