የሀገረ ስብከቱ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ በቺካጎ ተካሄደ፣ መጪው ጉባኤም በሚኒያፖሊስ እንዲሆን ተወሰነ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሰሜን ምሥራቅ፣ ደቡብ ምሥራቅ እና መካከለኛው አሜሪካ ኒውዮርክ ሀገረ ስብከት ዓመታዊ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ በሀገረ ስብከቱ ውስጥ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች፣ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደር እና የሰንበት ትምህርት ቤት ተወካዮች በተገኙበት ከኅዳር ፲፬ እስከ ኅዳር ፲፭ በቺካጎ ከተማ ተካሄደ።

ይህ ጉባኤ ሐሙስ ጠዋት ኅዳር ፲፭ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. በቺካጎ ደብረ ኤዶም ደብረ ገነት ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ካቴድራል በብፁዕ አቡነ ዘካርያስ መሪነት ጸሎተ ኪዳን በማድረስ እንዲሁም የዕለቱን ወንጌል ሉቃስ ወንጌል ምእራፍ ፪፣ ፵፩ - ፶፪ ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ ተርጉመው በስፋት ካስተማሩ በኋላ በሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪጅ ሊቀ ማእምራን ቀሲስ ዶ/ር ሙሴ ሐረገወይን አወያይነት ጉባኤው ተከፍቷል።

በቅድሚያም በ35ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ በጥቅምት 2009 ዓ.ም. በሀገረ ስብከታችን ተወክለው የተገኙት መልአከ ብርሃናት ቆሞስ አባ ማርቆስ ረታ (ርዕስ አድባራት ደብረ ብርሃን ቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል፣ ኦሃዮ) እና መልአከ አርያም ቆሞስ አባ ኃይለ ሚካኤል ሙላት (ርዕስ አድባራት ጽርሐ አርያም ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፣ ሚኒሶታ) ወጪያቸውን የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ሸፍነው በመሄድ የሀገረ ስብከታችንን ዓመታዊ የሥራ እንቅስቃሴ ያቀረቡት ሪፖርት ለዚህ ጉባኤ በሊቀ ማእምራን ቀሲስ ዶ/ር ሙሴ ሐረገወይን - የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪጅ አማካኝነት በንባብ ቀርቧል።

ጉባኤው ለሁለት ቀናት በተለያዩ ዐበይት ጉዳዮች ላይ ከተወያየ በሁዋላ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አስተላልፏል።

የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ በሀገረ ስብከታችን ተግባራዊ ስለማድረግ

በየጊዜው ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያስተላልፋቸውን ውሳኔዎች ተግባራዊ ለማድረግ በተለይም የአብያተ ክርስቲያናትን አንድነት ለማጠናከር ሀገረ ስብከቱ በወሰዳቸውን እና በሚወስዳቸውን እርምጃዎች የቅዱስ ሲኖዶስን ጥሪ በመቀበል በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ያላሰለሰ ጥረት በእናት ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ሥር ያሉ አብያተ ክርስቲያንት 33 የደረሱ ሲሆን እነሱንም ለማጠናከር እና ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ያልገቡትንም በሂደት እንዲገቡ ለማድረግ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ተጠናከሮ መቀጠል እንዳለበት የጋራ ስምምነት ላይ ተደርሷል።  በተጨማሪም  በሀገረ ስብከታችን የሚታየውን የብፁዓን አባቶች፣ የአገልጋይ ካህናት እና ሰባኪያነ  ወንጌል ጣልቃ ገብነት ሥርዓት የጣሰ አካሄድን ለቤተ ክርስቲያን አንዱ ፈተናዋ መሆኑን ጉባኤው በአጽንዖት አስምሮበታል።  በመሆኑም ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔዎችና የሀገረ ስብከቱን መመሪያዎች ተግባራዊ እንዲያርጉ ሆኖ ለዚህም የየአጥቢያው አስተዳዳሪዎች ግንባር ቀደም ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።

ስለ ሀገራችን ኢትዮጵያ እና ስለ ቤተ ክርስቲያን ሰላም እና አንድነት

ሀገራችን ኢትዮጵያ ሀገረ እግዚአብሔር በመሆኗ ከጥንት ጀምሮ በእግዚአብሔር ታምና እና ሰላሟንም ከእግዚአብሔር ብቻ እየጠየቀች ኖራለች። «እስመ በጸሎተ ጽድቅ ትድኅን ወኢትማስን አገር - በጻድቅ ጸሎት ሀገር ትድናለች፣ አትጠፋምም» እንዳለ ቅዱስ ሲኖዶስም «ስለ ሰላም ጸልዩ» ብሎ ያወጀው ይህንን መሠረት አድርጎ ነው። በመሆኑም በሀገረ ስብከታችን ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ከነሐሴ ፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም. ጀምሮ ስለ ሰላም ጸሎተ ምሕላ እያደርግን እንገኛለን። ይህም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባው ግንዛቤ ተወስዷል። «ኢትዮጵያ ታበጽህ እደዊሀ ኀበ እግዚአብሔር - ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች» መዝ ፷፰-፴፩ እንዳለ እጆቻችንን ወደ እግዚአብሔር እንጂ ወደ ሌላ በመዘርጋት ሰላምን ልናገኝ አንችልንምና አሁንም ፍጹም ሰላምን ወደሚሰጥ ወደ እግዚአብሔር በመዘርጋትና የቤተ ክርስቲያኗን ሐዋርያዊ ተልዕኮ ብቻ እያስፈጸምን ምእመናን ማገልገል እንደሚጠበቅ ተገልጿል።

በወረዳ ቤተ ክህነት ትይዩ ስቴቶችን ስለማዋቀር

በአሁኑ ወቅት ባለው አደረጃጀት እያንዳንዱ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ያላቸው ግንኙነት በቀጥታ ከሀገረ ስብከቱ ጋር በመሆኑ ምክንያት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የሠላሳ ሦስቱንም አብያተ ክርስቲያናት ጉዳይ በቀጥታ መከታተላቸው ከቃለ ዓዋዲውም አንጻር አግባብ ባለመሆኑና እና ለሥራ ቅልጥፍናም ስለማይረዳ ሀገር ቤት ባለው አሥራር በወረዳ ቤተ ክህነት ትይዩ የሆነና አጎራባች ስቴቶችን ያቀፈ መዋቅር ተሠርቶ ሥራ ላይ ቢውል የግንኙነት መሥመሩን የተቀላጠፈ ስንደሚያደርገው የታመነ ስለሆነ በየስቴቱ ያሉ አብያተ ክርስቲያናትን ብዛት እና ቅርበታቸውን አጥንቶ እንዲያቀርብ ከሀገረ ሥብከቱ ሥራ አስፈጻሚ በተጨማሪ ሁለት አባላት በሥራ አስፈጻሚው ተሰይመው መዋቅሩን አጥንተው  እስከ ጥር ፲፩ ቀን ፳፻፱ (ጥምቀት) አጠናቅቆ በቴሌ ኮንፈረንስ ለውይይት እንዲያቀርብ ተወስኗል።

የስብከተ ወንጌል አገልግሎትን ስለማስፋፋትና ሥርዓቱን የጠበቀ ስለማድረግ

ወደ ሀገረ ስብከታችን የሚመጡ ሰባኪያን አመጣጣቸው ሥርዓትን የጠበቀ ሆኖ፣ በሀገረ ስብከቱ ትምህርት ክፍል ዕውቅና አግኝቶ ቢሆን መንፈሳዊነትን ያልለቀቀ የወንጌል ትምህርት ለምእመናን ለማዳረስ ይረዳል። ይህ ሥርዓት የጠበቀ አሠራር በሁሉም አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ተግባራዊ ባለመሆኑ ትክክለኛውን የወንጌል አገልግሎት የሚሰጡ ሰባኪያን እንዳሉ ሁሉ የራሳቸውን ፍላጎት ለማሟላት፣ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ከወንጌል ውጭ የሚጓዙ፣ ከንቱ ተወዳጅነትን ለማትረፍ የሚጥሩ መምህራን እንዳሉም የጉባኤው ተሳታፊ የጋራ ግንዛቤ አግኝቷል። ስለሆነም ይህንን ነቅቶ የመጠበቅ ኃላፊነት ደግሞ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች እና የስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊዎች መሆኑ ታምኖበታል። ወደፊት የሀገረ ስብከቱ ትምህርት ክፍል የአብያተ ክርስቲያናትን መርሃ ግብር ያገናዘበ የሰባኪያንን የስብከተ ወንጌል ስምሪት የዓመት መርሃ ግብር ለማዘጋጀት ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የስብከተ ወንጌል ኃላፊዎች ጋር በመመካር ቢሰሩ ችግሩን ሊያቃልል ይችላል ተብሎ ታምኖበታል።

ስለተወገዙ ካህናት እና አብያተ ክርስቲያናት፣ በሀገረ ስብከትም ጣልቃ ስለመግባት

በሀገረ ስብከታችን እየተፈጸመ ያለውን ጣልቃ ገብነት አስመልክቶ ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ውጪ የሚደረጉ ተግባራትን በማውገዝ ቅዱስ ሲኖዶስ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ የሀገረ ስብከታችን ሊቀ ጳጳስ በተደጋጋሚ ባሳሰቡት መሠረት የተወሰነውን የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ለጉባኤው ተሳታፊዎች በንባብ ካሰሙ በሁዋላ በአጀንዳው ዙሪያ ውይይት ቀጥሏል። በውይይቱም ወቅት በውሳኔው ደብዳቤ ላይ እንደተገለጠው ብፁዕ አቡነ ዳንኤል ራሱን ከቤተ ክርስቲያን አስተዳድር እና ሥርዓት ውጪ ባደረገ ቦታ ተገኝው ለተወገዙ ካህናት ሹመት በመስጠት፣ የአዲስ ቤተ ክርስቲያን የመሠረት ድንጋይ በማስቀመጥ፣ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ በመጣስ ጣልቃ ገብነታቸውን አጠናክረው የቀጠሉበት ስለሆነ በዚህም የቤተ ክርስቲያንን የአንድነት ጉዞ በእጅጉ እየተፈታተኑ መሆኑን ጠቅላላ ጉባኤው በታላቅ ሐዘን ተመልክቶታል። ይህም ምእመናን ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን ከማቅረብ ይልቅ ይባስ እንዲደናገሩ እና በብፁዓን አባቶች ላይ ያላቸውን አመኔታ እንዲያጡ በማድረጉ ይህንን ጠንክሮ መዋጋት እንደሚገባ ስምምነት ላይ ተደርሷል። ስለሆነም ይህንን በተደጋጋሚ የፈጸሙትን የሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ጥሰት ተመልክቶ ቅዱስ ሲኖዶስ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ ሀገረ ስብከቱ ከጻፈው ደብዳቤ በተጨማሪ ይህን በሚመለከት የዚህ ጉባኤ የአቋም መግለጫ በደብዳቤ ለቅዱስ ሲኖዶስ እንዲጻፍና በአስቸኳይ እንዲላክ ወስኗል። ይህ የሚጻፈው ደብዳቤም ከዚህ ቃለ ጉባኤ ጋር ተያይዞ በሰነድነት እንዲቀመጥ ጉባኤው ወስኗል።


በመጨረሻም የሚቀጥለው ጉባኤ በሚኒያፖሊስ ርዕሰ አድባራት ጽርሐ አርያም ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አስተናጋጅነት ሐምሌ ፲፬ እና ፲፭ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. (July 21 እና 22, 2017) እንዲካሄድ ጉባኤው ተስማምቷል። ጉባኤውም አርብ ኅዳር ፲፮ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ በጸሎት ተጠናቋል።