የኒውዮርክ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ምእመናን እና ካህናት 1.6 ሚሊዮን ብር አዋጥተው ወደ ምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት በመላክ የብፁዕ አቡነ ዘካርያስ ቃል እንዲከበር አደረጉ።

+++

ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በነበሩበት ወቅት በሥራ ሂደት በጠፋው አንድ ሚሊዮን ስድስት መቶ ሺህ ብር ምክንያት በጊዜው የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ በነበሩት እና በሌሎችም ላይ ክስ በተመሠረተበት ወቅት ተከሳሾች በሰጡት ቃል «መንፈሳዊ አባታችን ስላዘዙን ወጪ አድርገናል» በማለታቸው ብፁዕነታቸው «ኃላፊነቱን እኔ እወስዳለሁ፣ የጠፋውንም ገንዘብም ከምእመናን ልጆቼ ለምኜ እከፍለዋለሁ» ማለታቸውን የአገር ውስጥና የውጪ ዜና አውታሮች ዘግበውት እንደነበረ የምናስታውሰው ነው።

የብፁዕነታቸውን ቃል ተግባራዊ ለማድረግ በሀገረ ስብከታቸው የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ምእመናን እና ካህናት ያዋጡትን አንድ ሚሊዮን ስድስት መቶ ሺህ ብር ይዘው የመጡት የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን / ሙሴ ሐረገወይን እና የሚዲያና ኮሚዮኒኬሽን ክፍል ኃላፊ አቶ ሠናይ ምንውየለት ረቡዕ ሚያዚያ ፳፭ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ ሪፖርት አቅርበዋል። በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በተመራው በዚህ ስብሰባ የወቅቱ የቋሚ ሲኖዶስ አባላት የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ፣ ብፁዕ አቡነ ጤሞቴዎስ፣ ብፁዕ አቡነ ጎርጎሬዎስ፣ ብፁዕ አቡነ ኢሳይያስ፣ ብፁዕ አቡነ ያሬድ እንዲሁም የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ማርቆስም በስብሰባው ተገኝተዋል።

የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን / ሙሴ ሐረገወይን ብፁዕነታቸው በሰሜን አሜሪካ እያደረጉ ስላሉት ታላቅ መንፈሳዊ ተጋድሎ በንባብ ያሰሙ ሲሆን ቅዱስ ፓትርያርኩ እና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ለብፁዕ አቡነ ዘካርያስ ያላቸውን አድናቆት እና ክብር የገለጹ ሲሆን ይህ ጉዳይ ከዳር በመድረሱ እና እልባት በማግኘቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

 

                    ==========  ለዝርዝሩ ቪዲዮውን ይመልከቱ ===========