ለአይዋ የመጀመሪያው ለኒውዮርክ ሀገረ ስብከት 34ኛ የሆነው ደብረ ሰላም ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ተተከለ

ለአይዋ የመጀመሪያው ለኒውዮርክ ሀገረ ስብከት 34ኛ የሆነው ደብረ ሰላም ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን ተተከለ

  • በዲሞይን አይዋም በግዛቱ ሁለተኛውን ቤተ ክርስቲያን ለመተከል የመጨረሻው ምእራፍ ላይ ይገኛሉ

በአይዋ ግዛት ሱ ሲቲ ከተማ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናን ከሀገረ ስብከቱ ጋር በመተባባር ለመጨረሻው ምእራፍ ያደረሱት የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን በሀገረ ስብከታችን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ መልካም ፈቃድ ዛሬ ቅዳሜ የካቲት 10 ቀን 2010 ዓ.ም. በመልአከ አርያም ቆሞስ አባ ኃይለሚካኤል ሙላት የሚኒያፖሊስ ርዕሰ አድባራት ጽርሐ አርያም ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አስተዳዳሪ ቅዳሴ ቤቱ ተከበረ። በዚህ በዓል ላይም የከተማው ምእመናን እስከዛሬ ድረስ ለሁለት ሰዓት የመኪና ጉዞ እየሄዱ አገልግሎት ያገኙ የነበረበትና ለአሁኑ ውጤትም ትልቅ አስተዋጽዖ ያበረከቱት የሱ ፎልስ ሳውዝ ዳኮታ ደብረ መንክራት ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ መንክራት ቀሲስ አበበ ላመስግን እንዲሁም ሊቀ ብርሃናት ቀሲስ ሄኖክ ያሬድ ከርዕሰ አድባራት ጽርሐ አርያም ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፣ ቀሲስ ምዑዝ ከዲሞይን አይዋ የኤርትራ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተገኝተዋል።

የሱ ሲቲ ምእመናን የራሳቸው የሆነ ቤተ ክርስቲያን ይኖራቸው ዘንድ ተደጋጋሚ ሙከራ ያደረጉ ቢሆንም እግዚአብሔር የፈቀዳት ይህች ቀን ስትደርስ ከፍጻሜ ሊደርስላቸው በቅቷል። የምእናኑን ፍላጎት ለራሳቸው ጥቅም ማስፈጸሚያ የሚጠቀሙ አንዳንድ አገልጋዮች እንደ ሱ ሲቲ አይነት ትናንሽ ከተሞች በመሄድ ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ውጪ ሀገረ ስብከቱ የማያውቃቸው አብያተ ክርስቲያናትን በመክፈትና እንደራሳቸው ፈቃድ በመጠቀም ምእመናንን እያደናገሩ የሚገኙ ሲሆን፣ የሱ ሲቲ ምእመናንም የዚህ አይነቱ አካሄድ ሰለባ ሆነው ለተወሰነ ጊዜ የቆዩ ነበሩ። አገልጋይ ነኝ ብለው የተቀመጡት ካህን ተግባር ከለመዱት ዉጪ የሆነባቸው ምእናን ጉዳዩን ለሀገረ ስብከቱ በማሳወቃቸው ክትትሉን የጀመረው የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት እኒህ ካህን ከቦታ ቦታ እየሄዱ ቤተ ክርስቲያንን የበደሉና በስሟ የሚነግዱ በመሆናቸው በሀገረ ስብከቱ ድጋፍ ሁኔታዎች መሥመር በማስያዝና እንደ አዲስ ሁሉንም ነገር በማሟላት አገልግሎት እንዲያገኙ አድርጓል።

የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ታቦትም ከሀገራችን ከኢትዮጵያ በብፁዕ አቡነ ዘካርያስ ተባርኮ በመልአከ አርያም ቆሞስ አባ ኃይለሚካኤል እና ለቦታው አገልጋይ በሆኑት ቀሲስ ለገሠ ይረፉ በኩል የሱ ሲቲ ሕዝበ ክርስቲያንን ይባርክ ዘንድ ለምእመናኑ ተልኮላቸዋል።