« ኢታርምም ወኢትደመም እግዚኦ - ጌታ ሆይ ዝም አትበል አቤቱ ቸልም አትበል» መዝ ፹፪(፹፫)፣፩ « እስመ ናሁ ዘአንተ ሠራዕከ እሙንቱ ነሠቱ - ምክንያቱም አንተ የሠራኸውን ሕግ እነርሱ አፍርሰውታልና» መዝ ፲(፲፩)፤፫

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ሲኖዶሳዊ አቋም በመጻረር በዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢዋ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን በማይፈቅደው መልኩ ያለ ቅዱስ ሲኖዶስ እውቅና እንመሠርታለን ስለሚባለው ማኅበረ ካህናት የሚመለከት ይሆናል።


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ በየዘመኑ በውስጥም ሆነ በውጭ አካላት በሚነሡ የተለያዩ ችግሮች ስትፈተን ኖራለች፤ አሁንም በመፈተን ላይ ትገኛለች። እውነተኛና ቀጥተኛ መንገድን ተከትላ የምትኖር ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በየዘመናቱ ስትፈተን ብትኖርም በፈተና የተሸነፈችበት ጊዜ ግን እስከ ዛሬ ድረስ በታሪኳ አልገጠማትም። አባቶቻችን ወደር በማይገኝለት ትዕግሥታቸው ከጸሎትና ከእንባ ጋር አምላካቸውን ተማጽነው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከእራስዋ ልጆች ሊቃነ ጳጳሳት በመሾም አሁን ለደረሰችበት ደረጃ እንድትበቃ አድርገዋታል። ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከእራስዋ ልጆች ፓትርያርክ መርጣ እና በየሀገረ ስብከቱም ሊቃነ ጳጳሳት መድባ በገጠርም ሆነ በከተማ ያሉ ልጆቿ በአንድ የቅዱስ ሲኖዶስ ጥላ ተሰባስበው ሃይማኖታቸውን በመጠበቅና በማስጠበቅ እንዲኖሩ በማድረግ የከፈለችው መሥዋዕትነት ከፍተኛ ነው።

በመሆኑም ይኽንን አንድነት አጥብቃና አጠናክራ እንድትቀጥል ከቅዱስ ሲኖዶስ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር መዋቅር በመዘርጋት በሃይማኖት ትምህርቷም ሆነ በአስተዳደሯ ችግር እንዳይገጥማት አበው በደነገጉት መመሪያ መሠረት በመመራት ላይ ትገኛለች። ከእንዲህ ያለው የአስተዳደር ሥርዓት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ከመስመር የሚወጡትን ቅዱስ ሲኖዶስ አካሄዳቸውን እየመረመረ ወደቀደመውና ወደተዘረጋው የሥርዓት መንገድ እንዲገቡ ሲያደርግ ቆይቷል፤ በማድረግም ላይ ይገኛል። በውጭው ዓለም የሚኖረው የሕዝብ ክርስቲያኑ ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ እንዲህ ያለው አሠራር በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአውሮፓም ሆነ በሰሜን አሜሪካ እንዲሁም በሌሎች የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ባሉበት ቦታ ሁሉ እየተዘረጋ ሀገረ ስብከት ተቋቁሞ አብያተ ክርስቲያናት በሊቃነ ጳጳሳት እየተባረኩና እየተመዘገቡ ከቀድሞው በተሻለ መልኩ መንቀሳቀስ ጀምረዋል። ይኽን ጅምር ለማስፋፋትና ለማሳደግ እያንዳንዱ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ ግዴታና ኃላፊነት አለበት። በተለይም ቤተ ክርስቲያኒቱ ሥልጣነ ክህነት ሰጥታ በእረኝነት ቦታ ያስቀመጠቻቸው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ መምህራነ ወንጌል፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እና ዲያቆናት ከሌሎች በተሻለ መልኩ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሃይማኖት፣ ሥርዓት፣ ቀኖና እና አስተዳደር ጠብቀው የማስጠበቅ ኃላፊነት አለባቸው።


እንደሚታወቀው ቤተ ክርስቲያናችንን ለማሳደግና ሃይማኖቷን ለማስፋፋት የተለያዩ የአገልግሎት ማኅበራት በየቦታው የተቋቋሙ ቢሆንም እንደሚሰጡት የአገልግሎት ስፋት ተጠሪነታቸው ለየሀገረ ስብከታቸው ሆኖ እውቅናን ያገኙ እንጂ በራሳቸው መንገድ የሚጓዙ አይደሉም። ቅዱስ ሲኖዶስ የማያውቀውና በሀገረ ስብከት ያልታቀፈ የካህናት ማኅበር ማቋቋም ግን ፍጹም አጠያያቂ እና ትክክለኛ ያልሆነ ጉዞ በመሆኑ ከወዲሁ እርምት ሊሰጠው ይገባል። በሃይማኖት ሥርዓቷ ዓለምን ያስደመመች ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በየትኛውም ስፍራ ቅዳሴዋ፣ ስብከቷ፣ ምስባኳና መዝሙሯ አንድ ዓይነት ሆኖላት ሰማያዊ ምስጋና ስታቀርብ ማየቱ የሰው ሥራ ሳይሆን የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ነውና እግዚአብሔርን ለማገልገል የተመረጠች አገር ሆና በምድር ላይ ሰማያዊ ሥርዓት እያከናወነች መገኘቷ እኛ በውስጧ የምንኖረውን ብቻ ሳይሆን ከእኛ ሃይማኖት ውጪ ያሉ ሁሉ ሲገረሙባት እናስተውላለን።

የፈተና መምጫው መቼና ከየት  እንደሆን አይታወቅምና በቀድሞው መንግሥት ከቅዱስ ሲኖዶስ እውቅና ውጪ « መላው የኢትዮጵያ ካህናት ማኅበር (መ/ኢ/ካ/ማ)» የሚባል ድርጅት ተቋቁሞ እንደነበር በታሪክ ብቻ የምናውቀው ሳይሆን የዓይን ምስክርም በመሆናችን ጉዳዩን በስፋት እናውቀዋለን። ይኽ መ/ኢ/ካ/ማ በመባል የሚታወቀው ማኅበር እንደ ሙያ ማኅበራት እንደ አንዱ ሆኖ ተጀምሮ ወደፊት የሚያመጣው ችግር አደገኛ መሆኑን በማወቅ ሳይውል ሳያድር መፍትሔ እንዲገኝለት ሦስተኛው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አስቸኳይ ስብሰባ በመጥራት የጉዳዩን አሳሳቢነት ለሊቃነ ጳጳሳቱ ይፋ አድርገው እርምት እንዲሰጥበት አድርገዋል። በመልእክታቸውም የቅድስት ቤተክርስቲያናችንን አካሄድ ሊያዛባ የሚችልና እኛ ሥራውን ልንከታተለው የማንችለው በራሱ የሚመራ የካህናት ማኅበር ሊቋቋም ስለማይገባው እንዲህ ያለው አካሄድ ስር ሳይሰድና ወደፊት ብዙዎችን በዚህ መረብ ውስጥ እያስገባ እንዳያጠምድ ከወዲሁ መገታት ስለሚኖርበት ይኼንን የተዛባ መንገድ እንቃወመዋለን፤ እናወግዘዋለንም በማለት ውሳኔ እንዲሰጥበት አስደርገዋል። በተላለፈው ሲኖዶሳዊ ውሳኔ መሠረትም የሚመለከተውን የመንግሥት አካል በማነጋገር ቅዱስ ሲኖዶስ ከአመሠራረቱ ጀምሮ የማያውቀውን ማኅበረ ካህናት (መ/ኢ/ካ/ማ) ማስቆም ችሏል። ቅዱስነታቸው ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጋር መክረው ይኽንን አደገኛ ጎዳና ያስቆሙት የካህናትን ኅብረት በመቃወም ሳይሆን ሰንሰለት የሌለውና እርከኑን ያልጠበቀ አካሄድ ነገ የሚያመጣውን ችግር በመመልከት ነው። 

ዛሬም አንድነት ፈጥረን ኅብረት ኖሮን እንቁም በሚል ሰበብ በሰሜን አሜሪካ በተለይም በዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ ያሉ እና በእኛ ሀገረ ስብከትም ያሉ የዚሁ ስሜት ተጋሪ ከሆኑ አንዳንድ ካህናት ጋር በመሆን እየተመሠረተ ያለው ማኅበረ ካህናት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የማታውቀው በመሆኑ መሥራቾቹ አካሄዳችሁን ከወዲሁ ሊገቱ እና እርምት ሊሰጡበት ይገባል። መሰባሰቡ ባይከፋም ይኽንን የካህናት ማኅበር ሊቋቋም፣ ሊመራና ክትትል ሊደረግበት የሚገባው እንደ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አካሄድ ከቅዱስ ሲኖዶሱ በተመደበ ሊቀ ጳጳስ መሆን ይገባዋል እንጂ ከላይ ከላይ የተነገረ አመለካከቱ ብቻ ቀና ነው በሚል ሰበብ ቀዳዳ ማበጀት ተገቢ አይደለም። እርከኑን የጠበቀ መሪ ሳይኖረውና ተጠሪነቱ ለማን እንደሆን ሳይታወቅ ማኅበር መመሥረት ያለ ምንም ጥርጥር ነገ ለብቻዬ መቆም ችያለሁ በሚል አንድምታ ለቅዱስ ሲኖዶስ የማይታዘዝ አካል መሆኑ አይቀሬ ነውና።በእድሜም በሥልጣንም ልጆቼ የምትሆኑ ካህናት ሆይ! ለብቻ ማኅበር መሥርታችሁ ለመቆም ለምን ፈለጋችሁ? ስል በቁጣ ሳይሆን በአባትነት እጠይቃችኋለሁ።

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከልጆቿ ከካህናት የበለጠ ከማን እርዳታን ትጠብቃለች? ማንንስ አደራ ትላለች? በውጭው ዓለም ያሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች እንግዳ በሆነ ትምህርት እየተወሰዱና ከቤተ ክርስቲያኒቱም ሥርዓት እየወጡ በሚታዩበት በዚህ ወቅት ብቸኛና አማራጭ የሌለው መፍትሔ በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ውስጥ ገብቶ አብሮ መሥራት ብቻ መሆኑ ለእናንተ የተሰወረ አይደለም። የእግዚአብሔር ቃል በይሁዳ መልእክት ቁጥር ሃያ አንድ እና ሃያ ሁለት ላይ «ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ። አንዳንዶች ተከራካሪዎችንም ውቀሱ፥ አንዳንዶችንም ከእሳት ነጥቃችሁ አድኑ።» ይላል። ይኽ መልእክት «እናንተ» እያለ አደራ ሰጥቶን እየሰማነው ሁላችን በየራሳችን መንገድ መጓዛችን ለምን አስፈለገን? እንዲህ ያለው አካሄድ የግል አካሄድ ከሃይማኖት መንገድ ወጥተው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን በውስጥም በውጭም ለሚዋጓት እድል ፈንታ የሚሰጥ በመሆኑ ይኽን አውቃችሁ ከግለኝነት መንፈስ እንድትወጡ እጠይቃችኋለሁ።

እንደ ቤተ ክርስቲያን አባትነቴ ልጆቼ ለምትሆኑ ለእናንተ ይኽንን መልእክት ሳስተላልፍ እኔም እናንተም ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ የተሰጠንን አደራ በጋራ መፈጸም እንድንችል ነው። ይህ አካሄድ ግን ሕገ ቤተ ክርስቲያንን በመተላለፋቸው ምክንያት ውግዘት የደረሰባቸው እና ክህነታቸው የተያዘባቸው ካህናት ይቅርታ እንጠይቃለን፤ በደብዳቤም እናሳውቃለን ብለው የገቡትን ቃል በማጠፍ መሸሸጊያ የሆናቸውን የገለልተኛነት መንፈስ ማዳበሪያ የሚሆን እና ቤተ ክርስቲያናችንን የሚጎዳ ተግባር ነው። መታዘዝ ከመሥዋዕት ይበልጣልና ሕጉ እንደሚያዘውና እንደሚፈቅደው መሄድ ሲገባ የግል ስሜት እንደሚፈልገው መሄድ ሃይማኖታዊ መንገድ ስላልሆነ መንጋውን የምትመሩ ካህናት እረኝነታችሁን አግባብ ባለው መንገድ እንድትወጡ በድጋሚ አደራ እላለሁ። በዚህ በዐብይ ፆም ሁላችንም ስለ ቤተ ክርስቲያን አንድነት እያሰብን በመፆም አባቶቻችን ያቆዩልንን ሃይማኖት ለተተኪው ትውልድ ለማስረከብ እንዘጋጅ። 

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመልክእቱ «ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ።» ፩ ቆሮ. ፩፡፲ በማለት እንዳስተማረን ቀድሞም የተለያዩትን አንድ ማድረግ የሐዋርያት ተልዕኳቸው በመሆኑ ልዩነትን አስወግደን በአንዲት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥላ ሥር በመሰማራት ማገልገል እንጂ ክህነትን እንደ ሙያ ብቻ በማየት በሙያ ማኅበር በመደራጀት ቤተ ክርስቲያንን በድጋሚ መበደል አግባብ አይደለምና ከእንዲህ ያለው ተግባር ታቅባችሁ በአንድነት እንድንቆም አሳስባችኋለሁ።

 

______

አባ ዘካርያስ
የኒዮርክ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክግልባጭ፦- ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት- ለቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት፣ ፣ አዲስ አበባ ኢትዮጵያ