ጉዳዩ፦ መጋቤ ሐዲስ እሸቱ ዓለማየሁን ይመለከታል

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የካህናት አገልግሎትን እና በሀገረ ስብከት ጣልቃ ገብነትን አስመልክቶ በወሰነው ውሳኔ መሠረት ማንኛውም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ሥር ያለ አገልጋይ ካህን፣ ሰባኬ ወንጌል፣ ጳጳስም ይሁን ቆሞስ በቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደር ሥር ባልሆነ በየትኛውም ቦታ መሄድ እንደማይችል፤ በአስተዳደር ሥር ወደሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ከመሄዱ በፊትም የሀገረ ስብከቱን ሊቀ ጳጳስ ፈቃድ ማግኘት እንደሚገባው፤ ይህንን ተላልፎ በሚገኝም ላይ ስለሚወደው ርምጃ መወሰኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አክብራና ቦታ ሰጥታ የሊቃውንት ማፍሪያዋ ከሆኑት ከፍተኛ ተቋማቶቿ በአንዱ መምህር አድርጋ የሰየመቻቸው መጋቤ ሐዲስ እሸቱ ዓለማየሁ በቅርቡ ወደ አሜሪካ አገር መጥተው «እዚህ ቦታ ለመምጣት ዋጋ ከፍየበታለሁ!» ብለው በገለጹትና በዳላስ በሚገኝው ከቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ውጭ በሆነ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስን ትዕዛዝ ተላልፈው ለመገኘታቸው መልስ እንዲሰጡ እየጠበቅን እያለ አሁንም በድጋሚ በእኛ ሀገረ ስብከት ውስጥ ወደሚገኝና በፍርድ ቤት ክስ መሥርቶ በገዛ ፈቃዱ ከቅዱስ ሲኖዶስ አስተዳደር ውጭ በሆነና የተወገዙ ካህናት እናገለግልበታለን በሚሉበት ቦታ ላይ ለማስተማር እንደሚመጡ ለማወቅ ችለናል።

እምነት እና ሥርዓትን ለደቀ መዛሙርት ከማስተማር በፊት አንድ መምህር ራሱ ሥርዓቱን እና ሕጉን ሳይከፍልና ሳይቀንስ ሊያምን እና ሊፈጽም ሲገባው መጋቤ ሐዲስ ግን ቤተ ክርስቲያኗ እና ምእመናን የሰጠቻቸውን የክብር ቦታ ለራስ ሃሳብ ማስፈጸሚያ ማዋልን መርጠዋል። ስለሆነም ለሁለት ተከታታይ ዓመታት በክብር ተስተናግደው በሄዱበት ሀገረ ስብከት ዛሬ ይህንን ለማድረግ የወሰኑበትን ምክንያት እንዲያስረዱ የተሰጣቸውን ዕድል ተጠቅመው እስኪያስረዱ ድረስና ይህንንም የሚገልጽ ደብዳቤ እስከሚደርሳችሁ ድረስ መጋቤ ሐዲስ እሸቱ ዓለማየሁ በሀገረ ስብከታችን ውስጥ ባሉ አብያተ ክርስቲያናት ማስተማር እንደማይችሉ ተገንዝባችሁ እርሳቸውን ከመጋበዝም ሆነ እንደዚያ ያለ ጉባኤ ከመሳተፍ እንድትቆጠቡ በአጽንዖት እናሳስባለን።  

ሙሉውን ለማንበብ PDF