መጋቤ ሐዲስ እሸቱ ዓለማየሁ ከአገልግሎት ታገዱ የሃያ አንድ ቀን የጊዜ ገደብም ተሰጣቸው


ለመጋቤ ሐዲስ እሸቱ ዓለማየሁ

ከአገልግሎት መታገድዎን ማሳወቅን ይመለከታል

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ፍጹም መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነ ትምህርትን በማስተማር የሐዋርያትን ትምህርት ትምህርቷ፤ የሐዋርያትን ሥልጣን ሥልጣኗ አድርጋ ከሁለት ሺህ ዓመታት በላይ ምሥጢራት ሳታፋልስና ከሥርዓት ሳትወጣ መኖር የቻለችው ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን ለመፈጸም የሚያስችለውን ምሥጢረ ክህነትን እና የሐዋርያዊ የአገልግሎት ሥምሪትን ሥርዓት ሠርታ እና አክብራ በመያዟ ነው። ይኽን ታላቅ ሥልጣን ለሐዋርያት የሰጠውም አምላካችን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከስፍራ ወደ ስፍራ በመዘዋወር ወንጌልን ሰብኮ፣ ተአምራትን አድርጎ፣ ዓለምን ከባርነት ነፃ አውጥቶ፣ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ ዘላለማዊ ድኅነትን ሰጥቶና ሥርዓትን አስተምሮ ያስተማራቸውን እንዲያስተምሩ፣ የነገራቸውን እንዲተገብሩ፣ ያዘዛቸውን እንዲፈጽሙና የዓለም ብርሃን ሆነው ይኽን ጨለማ ዓለም እንዲያበሩ እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል ሲልካቸው (ማቴ. ፲፡ ) እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ እኔ ሁልጊዜም ከእናንተ ጋር ነኝ። (ማቴ. ፡፳) በማለት ቃል ኪዳን ገብቶላቸው ነው።  የተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን የምትመራው በሕገ ሐዋርያት በፍትህ መንፈሣዊ ድንጋጌ ነው። ሕገ ወንጌል፣ የቅዱሳን ሐዋርያት መልእክት እና ሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍት፣ ሐዋርያት በየጊዜያቸው በደነገጓቸው ሲኖዶስ፣ አብጥሊስ፣ ድድስቅልያ፣ ቀሌምንጦስ፤ ግጽው፣ ሥርዓተ ጽዮን የተባሉት የቀኖና ሕጎችም መተዳደሪያዎቿ ናቸው። እነዚህ ሕጎች በሁሉም ቦታ ይተገበሩ ዘንድም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በውጭው ዓለም ላሉ አብያተ ክርስቲያናት ባስተላለፈው ጥሪ መሠረትና እኛም ባደረግነው መጠነ ሰፊ ተጋድሎ በሀገረ ስብከታችን የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን ተመልሰው፣ አዳዲሶችም ተመሥርተው፣ ለምእመናን ተስፋ የሚሆኑ ገዳማትም ተተክለው፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖትም በሀገረ ስብከታችን ተገኝተው ቡራኬ ሰጥተውን እና ሌሎችም ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ሥርዓቱን በጠበቀ እና የሀገረ ስብከቱን ልዕልና ባከበረ መልኩ እየተገኙ ቡራኬያቸውን እየሰጡን ምእመናንንም ባርከውልን ይሄዳሉ። 

በውጪው ዓለም ባለች ቤተ ክርስቲያናችን ራሳቸውን «ስደተኛ ሲኖዶስ» ብለው የሚጠሩ፣ እንዲሁም ደግሞ «ገለልተኛ ነን» የሚሉና ለቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የማይገዙ ካህናት ያሉበት በመሆኑ ይህ ሁሉ አገልግሎት ያለምንም ፈተና እየተከናወነ ያለ ግን አይደለም። በየጊዜው የሚገጥሙንንም ፈተናዎች ለቅዱስ ሲኖዶስ ማሳወቃችን እና ቅዱስ ሲኖዶስም ውሳኔ ያስተላለፈባቸው መሆኑ የሚታወቅ ነው። ይህንን እና መሰል ሁኔታዎችን ጠንቅቀው እያወቁ፣ እኔም ጊዜ ወስጄ አስረድቼዎትና ከሥርዓት ካፈነገጡ እምቢተኞች ጋር ሊተባበሩ እንደማይገባ ገልጨልዎት እያለ ትዕዛዜን እና ምክሬን አቃልለው ከውጉዛን ጋር መተባበርን መርጠዋል።

የእርስዎ ክብር የተመሠረተው «ተሠርታ ያለቀች!» እያሉ ለስብከት ማሳመሪያ ስሟን በሚያወድሷት ቤተ ክርስቲያን ክብር ላይ መሆኑን ዘንግተው ባለፉት ሳምንታት በአንድ ራስ ሦስት ምላስ በመሆን ሦስቱንም ዓይነት አስተዳደር እንከተላለን በሚሉ አብያተ ክርስቲያናት እየሄዱ ለእያንዳንዳቸው የሚመች የሚመቻቸውን እየመረጡ እየነገሩና እያስጨበጨቡ ይህች ተሠርታ ያለቀችዋን ቤተ ክርስቲያናችንን በሰላ አንደበት እና በቃላት ድርደራ የአንድነቷን ማገር በመሳብ እየፈጸሙ ያሉትን የአንዲት ቤተ ክርስቲያናችንን ሥርዓት የሚያቃልል ትምህርትዎን አጥብቄ አወግዘዋለሁ። «ችግሩ እስኪፈታ እና ሁኔታዎች እስኪስተካከሉ በያላችሁበት ቆዩ» እያሉ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን በማፋለስ ከቅዱስ ሲኖዶስ አስተዳደራዊ መዋቅር ውጪ ነን ብለው በቤተ ክርስቲያን ላይ ያመፁ ውጉዛን ካህናትን ማበረታታትዎትን እና ራሳቸውን «ስደተኛ ሲኖዶስ» ብለው የሚጠሩትንም እንደ ሕጋዊ አካል በመቀበል «ስደተኛ ሲኖዶስም አብያተ ክርስቲያናት ጋር ሄጄ አስተምሬአለሁ» ብለው እንደ ዝና የሚናገሩትንም ከንቱ ወሬ ቤተ ክርስቲያናችን እንዲህ ብላ አታምንምና አጥብቄ እኮንነዋለሁ!

«መከፋፈሉን ለማጥፋት ዋጋ መከፈል አለበት። ይህንን ልዩነት ለማጥፋት እኔ ፈንጅ ላይ ተንከባልያለሁ። እኔ የአቅሜን አድርጌያለሁ ውጪው ሲኖዶስ ሄጄ አስተምሬአለሁ፣ እዚህም (የተወገዙ ካህናት ያሉበት ገለልተኛ አስተዳደር) ስመጣ እንዲሁ ዋጋ ለመክፈል ብዬ ነው» ሲሉም ተደምጠዋል። ለእውነተኛ ሰባኬ ወንጌል ፈንጂ ላይ እንደ መንከባለል ይቆጠርለት የነበረው «ስደተኛው ሲኖዶስ» ነን ከሚሉት ዘንድ ሄዶ «ይህች ተሠርታ ያለቀች ቤተ ክርስቲያናችን በታሪኳ ያልደረሰባትን የስደት መንበር አታቋቁሙባት፣ ሕዝበ ክርስቲያኑም ከሚወዳት አገሩ ከኢትዮጵያ መሰደዱ ሳያንሰው ከሃይማኖቱም አታሰድዱት» ብሎ በድፈረት ማስተማር ነበር። ይህም ሳያንስዎት የተወገዙ ካህናት እናገለግልበታለን ወደሚሉት እና በፍርድ ቤት ክስ መሥርቶ ከቅዱስ ሲኖዶስ አስተዳደር ውጪ ሆኛለሁ ወዳለው የቀድሞው የሚኒያፖሊስ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ለመምጣት ማቀድዎን ስሰማ አስቀድሜ እኔው ራሴ ጊዜ ወስጄ ሁኔታውን አስታውቄዎት እያለ ቃሌን እና ትእዛዜን አቃልለው ሄዱ። በዚያም ቦታ ሄደው ሲያስተምሩ ፈንጅ ላይ እንደ መንከባለል የሚሆንልዎት የነበረው «አንድ ካህን ከተወገዘ በኋላ ቀድሶ ማቁረብ፣ አጥምቆም የሥላሴ ልጅነትን ማሰጠት አይችልምና ቀኝ እና ግራቸውን የማያውቁ የሕፃናት ልጆቻችሁን ክርስትና ለአፈ ጮሌ ደብተራ አሳልፋችሁ አትስጡ!» ማለት ነበር እንጂ ውጉዛን ካህናት በእግዚአብሔር ቅዱስ ሥጋ እና ክቡር ደም ሲያፌዙ አይዟችሁ ማለት ፈንጂ ላይ መንከባለል ሳይሆን ፈንጂ ማቀበል ነው። 

«አሁን አሜሪካ ውስጥ ያለው ችግር የሕዝብ ነው ብዬ አላምንም። አሜሪካን አገር ካህናቱ ናቸው የሚበጠብጡት። ራሳቸው አለቃ መሆን ስለሚፈልጉ በሆነ ምክንያት ጠብ ይፈልጉና አሜሪካ መቼም ቤተ ክርስቲያን መክፈት ሱቅ ከመክፈት ያነሰ ነው የሆነ ሱቅ ከፍቶ፣ ምእመናን ሰብስቦ ቀሲስ እንትና ይባልልናል። ቅስናውንም ጳጳሳቱ ለተሳለማቸው ሁሉ እንደ ሰንበቴ ዳቦ ያድሉታል። ይህንንም ቅስና ሕዝቡን ለመከፋፈል ይጠቀሙበታል። ለእነርሱ ክብር የዋሁን ምእመን እያራገፉ የሁለት እና የሦስት ሚሊዮን ዶላር ቤት እየገዙ ሕዝቡን ይበታትኑታል!» ሲሉም ተደምጠዋል። በእርግጥ ለአልፎ ሂያጅ መንገደኛ ይህን መናገር ቀላል ነገር ነው። እኒህ በመላ አሜሪካ በተለያዩ ስቴቶች ያሉትና እርስዎ የተሳለቁባቸው ካህናት ግን እንደ እርስዎ በዳላስ እና በሚኒያፖሊስ ተገኝተው ተራ የ «አንድ እንሁን» ወሬ በማውራት የተጨበጨበላቸው ሳይሆኑ በፍጹም መንፈሳዊ ድፍረት «ሐዋርያት ወደ ሰበሰቧት ወደ አንዲት እናት ቤተ ክርስቲያን መመለስ ይገባናል እንጂ ስደተኛ ሲኖዶስ፣ ገለልተኛ ቤተ ክርስቲያን እያልን ቤተ ክርስቲያንን ልናደማት አይገባንም!» ብለው በማስተማር የኖላዊነት ግዴታቸውን የተወጡ የሃይማኖት ጀግኖች ናቸውና እርስዎ በእነዚህ አደራቸውን በተወጡ ልጆቼ ላይ እንዲሳለቁባቸው አልፈቅድልዎትም! በይፋ ይቅርታ ሊጠይቋቸውም ይገባል!  እርስዎም በመጡ ጊዜ ሁሉ እኒህ «ሱቆች» ባሏቸው የሁለት እና ሦስት ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ባላቸው ቤተ ክርስቲያናት ያሉ ካህናት እና ምእመናን በኢትዮጵያዊ ባህል በክብር ተንከባክበው፣ እኒህ የተሳለቁባቸውና እኛም ሊቃነ ጳጳሳቱ እንደ ሰንበቴ ዳቦ ክህነትን አደሏቿው ያሏቿው ካህናት በዓመት ደመወዝነት እንኳን የማያገኙትን ገንዘብ ለእርስዎ ለአንድ ሰንበት አገልግሎትዎ እንደ ውሎ አበል ሰጥተው መሸኘታቸውን ረስተው ዛሬ ገና ለገና እርስዎ ከሌላ ማሳ ለመቃረም ስለፈለጉ ብቻ ትናንትና በክብር ያስተናገዱዎትን እና ኮሮጆዎትን የሞሉልዎትን ካህናትን መዝለፍዎ ከኅሊና በላይ ነው! 

«የእኛ ዘመን ጥሩ ዘመን እኮ ነው እግዚአብሔር አድሎን! እነ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ቢሆኑ ከሰበኩ በኋላ ጅራፍ ነበር የሚዘጋጅላቸው። ለእኛ ግን ድራፍት፣ ጥብስ ክትፎ ነው የሚዘጋጅልን። እኔ ጅራፍ የሚዘጋጅልኝ ቢሆን ኖሮ እንኳን አሜሪካ ሱሉልታም አልወጣም ነበር። አሁን አሜሪካ ድረስ የተንከራተትነው ከስብከቱ በስተጀርባ ዶላር ስላለ ነው። ይኼ ሁሉ መነኩሴ፣ ይኼ ሁሉ ጳጳስ አገሩን ትቶ የሚንከራተተው ከወንጌሉ ጫፍ ዶላር ነገር ስላለች ነው » ሲሉም ተደምጠዋል። እርግጥ ነው እርስዎም እንደመሰከሩት እርስዎ የመጡት «ሱቆች» ያሏቸው አብያተ ክርስቲያናት ፈተናውን ሁሉ አልፈው የመኸር ወቅታቸው ላይ ስለሆነ የዘረዘሯቸውን ሁሉ እኛ ዘንድ በመጡ ጊዜ በተራ አቅርበውልዎታል። ሆኖም ግን እኒህ የሚሳለቁባቸው ካህናት ሆነ እኔም ሊቀ ጳጳሱ እርስዎ ይህንን ከላይ ያለውን ተናግረው ባስጨበጨቡበት መድረክ «ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት፣ ሕጓም ሥርዓቷም ሊሸራረፍ አይገባም!» ብለን በማስተማራችን ጅራፍን ተቀብለንበታል፤ ሊቀ ጵጵስናችን እና ክህነታችን ተረስቶ «አንተ» ተብለንበታል፣ ክቡር ከሆነ ከቅዳሴ አገልግሎት በፖሊስ ተስተጓጉለንበታል፣ ከምድራዊ እና ከሰማያዊ ዳኛ ምረጡ ተብለን በፍርድ ቤት ተንከራተንበታል! ካህናት እና ምእመናንንም ለዓመታት ያፈሩትን በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እንደ ትቢያ አራግፈው እንዲሄዱ ተገድደውበታል! ለእርስዎ ያጨበጨበች እጅ በእኛ ላይ ግን ጅራፍን በመምዘዝ የሐዋርያትን ጥሪ ያሰማነውን እኛ ገርፎናልና የእርስዎ ወገንተኛነት ከማን ጋር እንደሆነ ራስዎን ይመርምሩ። 

በዳላስ «ስደተኛ ሲኖዶስ» ነን ከሚሉትም ሆነ በሚኒያፖሊስ የቀድሞው ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ውጉዛን ካህናት ጋር በአገልግሎት ከተሳተፉ በኋላ «ቅዳሴውን ሰምተናል፣ ሁሉንም ተመልክተናል። ከኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን አንድም የጎደለ ነገር አላገኘሁም። የልምድ አዋላጅ ሰባኪ፣ ከማዞሪያ ላይ የተሳፈርሁም አይደለሁም። ከሰባት ዓመቴ ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን ትምህርት ነው የኖርሁት። ሁሉን አውቀዋለሁ። አንድም የጎደለ ነገር የለም (የሚታይ ካልሆነ በስተቀር) አንድም የጎደለ የለም» ሲሉም ተደምጠዋል።

•      ከሰባት ዓመትዎ ጀምሮ ያስተማረችዎት ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስን መመሪያ ተላልፈህ ባልተፈቀደ ቦታ ቁም ብላ አላስተማረችዎትም፤

•      ከሰባት ዓመትዎ ጀምራ ያስተማረችዎ ቤተ ክርስቲያን ክብር ይግባውና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ክቡር ደም ከገበያ በሚገዛ የደምበጃን ወይን ሲተካ ይህ ምንም ችግር የለውም የጎደለ ነገር የለውም ብላ አላስተማረችዎትም፤ 

•      ከሰባት ዓመትዎ ጀምሮ ያስተማረችዎት ቤተ ክርስቲያን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የተአምሯ መጽሐፍ «የሚረብሽ መጽሐፍ ነው» በሚባልበት እና ስሟ በተነቀፈበት ቦታ መገኘት ምንም ችግር የለውም የጎደለ ነገር የለውም ብላ አላስተማረችዎትም፤ 

•      ከሰባት ዓመትዎ ጀምራ ያስተማረችዎ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ያሬድ የምስጋና ዝማሬ እና ቅዳሴያቱም በኦርጋን ቢቀርቡ የሚያጎድለው ነገር የለም የተሟላ ነው ብላ አላስተማረችዎትም፤  

•      ከሰባት ዓመትዎ ጀምራ ያስተማረችዎ ቤተ ክርስቲያን ከተወገዘ ካህን ጋር በአገልግሎት መሳተፍ፣ ሦስት እና አራት መሥመር እየዘለሉና የመንፈስ ቅዱስን ቃል እየሻሩ እንቀድሳለን ከሚሉት ጋር መተባባር ራስንም እንደሚያስወግዝ እንጅ ምንም የጎደለ ነገር የሌለበት ነው ብላም አላስተማረችዎትም። 

ይህንን ሁሉ ጥፋት እንዳያጠፉ አስቀድሞ የመከረዎትም ከ «ግማሽ ፌርማታ ላይ የተሳፈረ ካህን» ብለው እርስዎ ያንኳሰሱት ዓይነት ካህን ሳይሆን ውግዘቱን ያስተላለፍኩትና የእርስዎን ዕድሜ ያክል በሊቀ ጵጵስና ያገለገልሁ እኔ የክፍሉ ሊቀ ጳጳስ ሆኜ እያለ እርስዎ ግን ይህንን ምክሬን እና ትዕዛዜን ንቀው እና አቃልለው በመሄድ «ምንም ያጎደላችሁት የለምና በርቱ» ብለዋቸው ውጉዛኑን ካህናት አደፋፍረው የዋሁን ምእመንም ላይ ፈርደውበት ተመለሱ።

 «ወዳጆች ሆይ፥ ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ፥ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ። ከብዙ ጊዜ በፊት ለዚህ ፍርድ የተጻፉ አንዳንዶች ሰዎች ሾልከው ገብተዋልና» እንዳለ ይህንን ሥርዓት እና እምነት የሚያፋልሱትን ሁሉ ማንንም ከማንም ሳንለይ  የሚገባውን መልስ በመስጠትን እርምጃም በመውሰድ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እየተጋደልን እንገኛለን። 

በዚህም ምክንያት አንዳንድ ካህናት ከተወገዙ ካህናት ጋር እናገለግላለን በማለት ሥርዓትን እየጣሱ ሾልከው በመግባት የራሳቸውን ዓላማ ለማሳካት በሞከሩ ጊዜ ሁሉ ቀድሶ በማቁረብ፣ ጸሎተ እጣን አጥነው በማሣረግ መንጋውን ያገለግሉበት ዘንድ የተሰጣቸውን ክህነት ለትምክህትና ለእምቢተኛነት በመጠቀማቸው ምክንያት ያላከበሩትን ክህነታቸውን አግደንባቸዋል። ምንም እንኳን እርስዎም ባለዎት ክህነት እኒህን አገልግሎቶች መፈጸም ባይችሉም፣ እግዚአብሔር የሰጠዎትን የቃለ ወንጌል ዕውቀት ለእምቢተኛነት ስለተጠቀሙበትና ስለ ጉዳዩ ባነጋገርኩዎት ወቅትም «እሺ ይሁን» በማለት ፋንታ «እኔም እጅግ ብዙ ተከታዮች ስላሉኝ ማስጠንቀቂያ ደብዳቤው ሊጻፍብኝ አይገባም!» በማለት ያልተገባ እምቢተኛነትዎን አሳዩ። በእንዲህ ያለ የትዕቢት መንፈስ ካህናቱን እና ምእመናን እንዲያውኩብኝ ስለማልፈቅድ ከዛሬ ጀምሮ በእኔ ሀገረ ስብከት (በሰሜን ምሥራቅ፣ ደቡብ ምሥራቅና መካከለኛው አሜሪካ ኒው ዮርክ ሀገረ ስብከት) ባሉ በየትኛውም አብያተ ክርስቲያናት ማስተማር እንዳይችሉ የታገዱ መሆኑን ለአብያተ ክርስቲያናቱ አሳውቀናል፤ ለእርስዎም ይኸው ገልጸናል፤ ያስተማሩትንም አንሥተናል፤ ውድቅም አድርገናል። 

አንዳንድ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት የሰጠንዎትን የሃያ አንድ ቀናት ገደብ ተጠቅመው ይህንን ያኽል ድፍረት በመድፈርዎ ተጸጽተው እንዲመለሱና ላጠፉት ጥፋት በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቁ እያሳሰብን፣ ይህንን ባያደርጉ ግን ቀኖናው በሚፈቅደው መሠረት በጣልቃ ገብነት ገብተው ላጠፉት ጥፋት እና ቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያም ስሟ በተነቀፈበት ተገኝተው ምንም የጎደለ ነገር አልሰማሁም በማለትዎ፣ ምንም ዓይነት ሥልጣነ ክህነት ከሌላቸው እና ሦስት እና አራት መሥመር እየዘለሉና የመንፈስ ቅዱስን ቃል እየሻሩ እንቀድሳለን ከሚሉት ጋር ተባብረው በአገልግሎታችሁ ምንም ስህተት የለም ብለው የሐሰት ምስክርነት በመስጠትዎ ሥልጣነ ክህነትዎንም የምናግድ መሆኑን በአጽንዖት እናሳውቃለን። ይህንንም ለቅዱስ ሲኖዶስ ያስተላለፍን መሆኑን ጨምረን እናስታውቃለን። 

 

እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክ!

ግልባጭ፦

- ለስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ አዲስ አበባ፣ኢትዮጵያ