ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ ዘመን መለወጫን እና የሀገረ ስብከቱ ዌብ ሳይት መጀመርን አስመልክቶ ያስተላለፉት መልዕክት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

የተከበራችሁ በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጪም የምትኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ሁላችሁ! የዘመናት ጌታ የሆነው ጌታችን መድኃኒታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ከዘመነ ዮሐንስ ወደ ዘመነ ማቴዎስ በሰላም አደረሳችሁ እያልኹ ይኽንን የከበረ አባታዊ ሰላምታ አቀርብላችኋለሁ።

እንደሚታወቀው ሁሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊት፣ጥንታዊት እና ቀዳሚት በመሆኗ በራሷ የግዕዝ ቋንቋ፣ ባላትም የዘመናት መቁጠሪያ ቀመር እየቀመረች መጥቅዕ፣ አበቅቴ፣ አዝማናትን እና አጽዋማትን እያወጣች፣ በሊቃውንቶቿ አማካኝነት በገዳማት፣ በአድባራት፣ በደሴቶች፣ በገጠሩ፣ በሁሉም ላሉ ምእመናን ታድላለች። ይህ የዘመን መቁጠሪያ ይባላል። ዘመን ማለት አንድ ድርጊት የተፈጸመበት፣ አንድ ሥራ የተሠራበትና የተከናወናበት ያለፈውም የሚመጣውም ማለት ነው።

በዚህ የዘመን መቁጠሪያ አጽዋማት፣ በዓላት፣ አውራኅ፣ ዓመታት እና ቀኖች እነዚህ ሁሉ የሚውሉበት አጠናቅቀው ያውቁበታል። በዚህም የምኅላ ቀናት፣ የጸሎት ቀናት፣ የበዓላት ቀናት ብለው ለይተው ያውቃሉ፤ እግዚአብሔርንም ይማልዱበታል። ይህ በአጠቃላይ ትርጉሙ ባሕረ ሃሳብ ይባላል - የዘመናት ቁጥር ማለት ነው። ይህንንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች በሙሉ ሊያውቁት ይገባል። በዘመን ሂድት የሊቃውንት ማነስ ቢመጣ፣ ምእመናን ሁል ግዜ ትንሣኤ ዘጉባኤን ብቻ ተስፋ በማድረግ መኖር ሳይሆን ሁሉም ኦርቶዶክሳዊያን ጠንክረው ይኸንን ተምረው ከልቦናቸው መዝገብ ላይ ፈልገው ማግኘት ይኖርባቸዋል፤ የጥንት አባቶች እና እናቶች በእንዲህ ዓይነት ነበር የሚጠቀሙትና። ከዚህ ቀመር በፊት ይኖሩ የነበሩትም ችግራቸው ይህ ነበርና፦ ትንሣኤን እንደ ወሩ አቈጣጠር በማዞር ሰኞ፣ ማክሰኞ፣ ረቡዕ፣ ሐሙስ ያውሉት ነበር። ከዚህም የተነሣ ይሳቀቁ ነበር። ዐቢይ ጾምን ጾመው፣ ህማማትን ጀምረው፣ ትንሣኤ ሳይውል ጾመ ሐዋርያት ይመጣ ነበረ። በእግዚአብሔር ፈቃድና በሊቃውንቱ ጸሎት ይኽ ቀመር ሲሠራ ግን ትንሣኤ ከእሑድ እንዳይወጣ፣ እርገት ከሐሙስ እንዳይወጣ፣ ደብረ ዘይት ሆሳዕናና ጰራቅሊጦስ ከእሑድ እንዳይወጡ፣ ዐቢይ ጾምና ነነዌ ከሰኞ፣ ጾመ ድኅነት ከረቡዕ እንዳያልፉ ተወስኗል። በዚህም ምእመናኑ እየተጠቀሙ ይገኛሉ።

የተወደዳችሁ ምእመናን!

በዘመናቱ መካከል አንድ አንድ ጊዜ ክፉ ነገር ቢገጥም፣ መከራም ቢመጣ በተሰጡት ቀናት ማለትም በበዓላት፣ በአጽዋማትና በምኅላ ቀኖች በሱባኤ ወራቶች እግዚአብሔርን ከልብ በመለመን እግዚአብሔር ችግሩን መከራውን እንዲያርቀው  መለመን ነው እንጂ በእግዚአብሔር ላይ መማረርና መሳቀቅ እግዚአብሔርንም መውቀስ አይገባም። እግዚአብሔር ራሱ ባለቤቱ «ንዑ ንትዋቀስ - እኔ እና እናንተ ኑ እንወቃቀስ » ብሎ በኢሳይያስ በተናገረው መሠረት - ይኸውም ለምኑኝ ወደ እኔ ጸልዩ ማለት እንጂ ተከራከሩኝ ማለት አይደለም ። ሰው እግዚአብሔርን አንተ ታውቃለህ በማለት ሳይሆን በራሱ ፈቃድ የወቀሳ ነገርን በእግዚአብሔር ላይ ሲሰነዝር እግዚአብሔርም መልሱን ይሰጣል፤ ሳይቆጣም ያስረዳል። ለምሳሌ ያህል በባቢሎናዊያን መንደልቶ የተደበደበ ትሩፍ ፈጣሪውን እንዲህ ብሎ አማረረ «ምን ትብከ ተሃሉ ውስተ ሰማይ (ዘእንበሊየ) - ጌታዬ ሆይ አንተ በሰማይ ሆነህ እኔን ለምን አታስበኝም እንዲህ መከራ ስቀበል፣ ስቀጠቀጥ በሰማይ ያሉ መላእክትን ትጠብቃለህን? በመላእክት ላይ የቀን ወራሪ የሌሊት ሰባሪ አለባቸውና እነርሱን እየጠበቅህ ነውን» ብሎ ፈጣሪውን ለመውቀስ ሰንዝሯል። ጌታም መልሶ «ወምንተ እፈቅድ ሃቤከ ውስተ ምድር (ዘእንበሌከ) -  አንተስ በምድር ላይ ሆነህ ምን እየሠራህ እንደሆነ አውቅ የለምን? እኔን ፈጣሪህን አምላክህን ትተህ በምድር ያሉ እንሰሳትን አራዊትን፣ በምድር የሚሳቡትን ፣ በሰማይ ያሉ ፀሐይ ጨረቃ ክዋክብትን እያመለክህ አይደለምን? እንዴት አድርጌ ልስማህ?» ብሎ መልሱን ይሰጠዋል።» ይህ የሊቃውንቱ ጠለቅ ያለ ትርጉም ነው። መዝ. ፸፪(፸፫)፣፳፭

ከዚህም ሌላ ዕንባቆምም በጣም ተሳቅቆና ተማርሮ «አቤቱ፥ እኔ ስጮኽ የማትሰማው እስከ መቼ ነው? ስለ ግፍ ወደ አንተ እጮኻለሁ፥ አንተም አታድንም» ብሎ ተናግሯል። ዕንባቆም ፩፤፪። ስለሆነም በየጊዜው በየዘመኑ መከራ ሲገጥመን እግዚአብሔርን ይቅርታ ጠይቀን እኛም ከክፋታችን የምንመልስበትን መንገድ ማሰብ ይገባናል እንጂ መማረር፣ እግዚአብሔርን መውቀስ አይገባንም። በዚህ በዘመኑ ሁከት የሚነሳ፣ መከራ የሚገጥም ቢሆንም ወደ እግዚአብሔር መጸለይ ተገቢ ነው፤ ሁሉን የሚያርቀው እርሱ ነውና። ለዚህም ከሐዋርያት አብነት እንወስዳለን፦ «በዚያም ቀን በመሸ ጊዜ ወደ ማዶ እንሻገር አላቸው። ሕዝቡንም ትተው በታንኳ እንዲያው ወሰዱት፥ ሌሎች ታንኳዎችም ከእርሱ ጋር ነበሩ። ብርቱ ዐውሎ ነፋስም ተነሣና ውኃ በታንኳይቱ እስኪሞላ ድረስ ማዕበሉ በታንኳይቱ ይገባ ነበር። እርሱም በስተኋላዋ ትራስ ተንተርሶ ተኝቶ ነበር፤ አንቅተውም መምህር ሆይ፥ ስንጠፋ አይገድህምን? አሉት። ነቅቶም ነፋሱን ገሠጸው ባሕሩንም ዝም በል፥ ፀጥ በል አለው። ነፋሱም ተወ ታላቅ ፀጥታም ሆነ። እንዲህ የምትፈሩ ስለ ምንድን ነው? እንዴትስ እምነት የላችሁም? አላቸው። እጅግም ፈሩና እንግዲህ ነፋስም ባሕርም የሚታዘዙለት ይህ ማን ይሆን? ተባባሉ። » ማርቆስ ፬፣ ፴፭- ፍጻሜ።

አባቶቻችን ሐዋርያት በዚህ ቀን አልቀናቸውም ነበር። በቄሣሪያው ጎዳና ነሐሴ ፯ ቀን «ሰዎች እኔ ማን እንደ ሆንሁ ይላሉ?» ብሎ በጠየቃቸው ጊዜ ሁሉም እንደየአባባላቸው ሲመልሱ ዮሐንስ መጥምቅ፣ ኤልያስ፣ ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ይሉሃል ብለው ሲመልሱለት ኰኵሀ ሃይማኖት ቅዱስ ጴጥሮስ «አንተ ክርስቶስ የህያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ» ብሎ በመመስከሩ የመንግስተ ሰማይ ቊልፍ ተሸልሟል። ሆኖም ግን በዚህ ማዕበሉ በተነሳበት ቀን ግን ሁሉም ሐዋርያት ከእርሱ ጋር በመርከቡ ውስጥ ሆነው «ማን ይሆን? ማን ይሆን?» ከመባባል ያለፈ ምንም ያሉት ነገር የለም።

ብዙ ምእመናንን ያስተማረውና ያጠመቀው ዕረፍቱም የዘመን መለወጫ ዕለት የሆነው በርተሎሜዎስ «የተጠመቁት ሴቶች ሁሉ በቅድስና በንጽሕና ሆነው ፈጣሪያቸውን ሲያገለግሉ አንዲት ሴት ከአንድ ወንድ በስተቀር ከብዙ ወንዶች ጋር መሆን አይፈቀድም» ብሎ በማስተማሩ አግሪጳ የተባለው ንጉሡ ለምን ይህን ትላለህ ብሎ በማቅ ሸፍኖ በባሕር አስጥሎት በሀገራችን አቈጣጠር የዘመን መለወጫ ዕለት ሰማዕትነቱን፣ ምሥክርነቱን ፈጽሟል። ይህን ሰማዕትነት የተቀበለው በርተሎሜዎስ ግን በዚህ ማዕበሉ በተነሳበት ዕለት ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ «ማን ይሆን?» ከማለት በስተቀር ሌላ ያለው የለም። ኰኵሀ ሃይማኖት ጴጥሮስም ምንም ሌላ የተናገረው ነገር የለም። የነጐድጓድ ልጆች - ዮሐንስና ያዕቆብም አብረው እንደነበሩ መጽሐፉ ያስረዳል፤ ነገር ግን ምንም ያሉት ነገር የለም። ብዙ ባለሟልነት ያለው ነባቤ መለኰት ታዖሎጎስ ዮሐንስ እንኳን በዚያ ቀን የተናገረው ነገር የለም። እናም አባቶቻችን የሚናገሩበትና የሚመሠክሩበትም ጊዜ ኖሯቸው ይሁን ወይም ሌላ ይሁን አይታወቅም ሁሉም ምንም ያሉት ነገር አልነበረም። ነገር ግን እኔ በልቡናዬ እላለሁ «ምነው ጌታዬ ሆይ ከአንተጋር አብሬ በነበርኹና ‘አንተ ትኴንን ኃይለ ባሕር፤ ወአንተ ታረምሞ ለድምፀ ማዕበላ - አንተ የባሕር ኃይል አዛዥ ነህ ማዕበሉን ሞገዱን ፀጥ ለጥ ታደርገዋለህ’ ብሎ ዳዊት የተናገረውን ጠቅሼ አንተ የባሕር ኃይል አዛዥ የባሕሩን የሞገዱን ድምጽ ጸጥ የምታደርገው አንተ ነህ ብዬ በመሰከርኹ» ብዬ አስባለሁ መዝ ፹፰(፹፱)፣፱ ወይም ደግሞ የቤተ ክርስቲያናችን ልጆች በዘመናዊው ቋንቋ «You are master of the sea's strength, And You calm the surging of its waves» የሚለውን ጠቅሰው በመለሱ ነበር እላለሁ። ይኸውም የቤተ ክርስቲያናችንን ልጆች ዕውቀታቸውን እና ምጥቀታቸውን አርቆ በማሰብ ነው። ቅዱስ ማቴዎስም አብሮ ነበረ እርሱንም ላነሳው የፈለግሁት ዘመኑ ዘመነ ማቴዎስ ተብሎ ስለተነገረለት ነው። ስለሆነም በዘመኑ ሁሉ ሁከት ማዕበል ሲነሣ ማዕበላትን በሥልጣኑና በኃይሉ ጸጥ ረጭ ወደ ሚያደርገው ወደ አምላካችን እግዚአብሔር አጥብቀን ልንጮህ ይገባናል።

የተወደዳችሁ ምእመናን!

«ዘይትቃወሙ ለጊዜ ያኅሥር ርዕሶ - ዘመኑን፣ ጊዜውን፣ ወራቱን የሚቃወም ሰው ራሱን መቃዎሙ ነው ምክንያቱም ጊዜው አንተ እንዳደረግኸው ነውና፦ መልካም ብትሠራበት መልካም ነገር  ይመጣልኻል፣ ጠማማ ነገር ብትሠራበት ጠማማ ነገር ይመጣብኻል» ይላል አንጋረ ፈላስፋ። ስለዚህ ዘመኑ ቀና እንዲሆንልን፣ የተቃና ሆኖም የተቃና ነገር እንድንሠራበት እኛም ድርሻ እንዳለን ልንረዳ ይገባል። ጌታንም ራሱን «ወምስለ ብእሲ ንጹሕ ንጹሐ ትከውን፤ ወምስለ ኅሩይ ኅሩየ ትከውን፤ ወምስለ ጠዋይ ትጠዊ - ከጻድቅ ሰው ጋር ጻድቅ ትሆናለህ፣ ከንጹሕም ሰው ጋር ንጹሕ ትሆናለህ፤ ከጠማማም ጋር ጠማማ ትሆናለህ» መዝ. ፲፯(፲፰)፣ ፳፭-፳፮  ይላል። አሁን ጌታ ጠማማ የሚሆን ሆኖ አይደለም ሰውን እንደ ሥራውና እንደ ጠማማነቱ የጠማማነቱን ፍዳ ስለሚከፍለው እንዲህ አለ እንጂ። በዚሁ ዓይነት እየተጓዝን ሁላችንም የእግዚአብሔር ቃል እንድንማር ቃሉንም ሰምተን መንፈሳዊ፣ አምላካዊ እና ሰማያዊ ሥራ እንድንሠራ ትጋት እና ጥረት ማሳየት አለብን።

ስለሆነም ይህንን እና ይህንን የመሳሰለውን ሁሉ በሰፊው የምንማርበትና ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት የምንሰጥበት «መንገደ ሰማይ» የተሰኘ ዌብ ሳይት ሀገረ ስብከቱ አዘጋጅቷል። «ከሰማይ ካልተሠጠህ በስተቀር» ሲል ‘ከእግዚአብሔር ካልተሠጠህ በስተቀር’ ማለቱ እንደሆነ ሁሉ «መንገደ ሰማይ» ማለትም «መንገደ እግዚአብሔር» ማለት ነውና  በመንፈሳዊ መንገድ እንድንሄድ፣ በእግዚአብሔር መንገድ እንድንሄድ፣ እግዚአብሔርን እንድንከተለው «ተመሰሉ ኪያየ ቅዱስ ውእቱ - እኔ ቅዱስ እንደሆንሁ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ» እንዳለም እግዚአብሔርን እንድንመስለው የሚያስችሉንን ትምህርቶች የምንማርበት ዌብ ሳይት ነውና ሁላችሁም ትጠቀሙበት ዘንድ የተዘጋጀ ነው።

የእግዚአብሔር ቃል ሰው ያለ ራዕይ መኖር የማይችል መሆኑን ሲያረጋግጥ «ራዕይ ባይኖር ሕዝብ መረን ይሆናል» (ምሳ. ፳፱፣ ፲፰) ይላል። የሰው ልጅ ዓለምን በኃላፊነት ሊመራ ከእግዚአብሔር በአደራ የተቀበለ ባለ ራዕይ ነው። ከሰማይ እስከ ምድር፤ ከረቂቅ እስከ ግዙፍ፤ በሚታይና በማይታየው ፍጥረት ሁሉ የመጠቀም መብት የተሰጠው በእግዚአብሔር አምሳል ለተፈጠረው የሰው ልጅ ብቻ ነው። ከሥነ ፍጥረታት ሁሉ ሰውን የሚያልቀውና ልዩ፤ ክቡር ፍጥረት የሚያደርገው «ባለ አእምሮ» መሆኑ ነው። «እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ በተሰጠኝ ጸጋ እናገራለሁ»(ሮሜ ፲፪፣፫) እንዲል። በዘመናችን የሚታየው የሳይንስና የሥነ ቴክኖሎጂ ፍሰትም የዚሁ የሰው ልጅ አእምሮ ግኝት ነው። የትኛውም የሥነ ጥበብ ቴክኖሎጂ የበጎም የክፉም መገልገያ መሣሪያ ሊሆን ይችላል። ዓለምን አንድ መንደር ያደረገው መገናኛ ብዙኃን ሁሉ የሰው ልጅ እይታና ሀሳብ ማስተላለፊያ ሲሆን ጉዳቱና ጥቅሙ የሚለካው በአእምሮ ሚዛን ነው።አእምሮ በእውቀት፤ በእምነትና በማስተዋል የተዘጋጀ ከሆነ ራዕዩና ተልዕኮው በትክክል ግቡን ሊመታ ይችላል። ከዚህም የተነሳ ቴክኖሎጂ የእግዚአብሔር የጸጋ ፍሰትና የሰው ልጅ የእምሮ ምጥቀት መሆኑን እንረዳለን።

ዛሬ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች በአንድ ማዕድ ወንጌልን ይማራሉ። በዓለም ዙሪያ ያለች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልዕኮዋና የዕለት እንቅስቃሴዋ በአንድ ጊዜ በሁሉም ሥፍራ ይነበባል። ይኽም በብዙ መቶ ማይል ተራርቀው ላሉት ነፍሳት ብርታትና እድገት መሆኑ የሚታመን ነው። በመሆኑም ይኽ ድኅረ ገጽ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ራዕይንና ተልዕኮን የሚያንፀባርቅ፤ የሀገረ ስብከታችንን ወቅታዊ እንቅስቃሴ የሚያበሥር ሆኖ መንፈሳዊ ግልጋሎቶችን ለመስጠት የቆመ ነው።

የዚህ ድረ ገጽ ተቀዳሚ ዓላማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ራዕይንና ተልዕኮን መፈጸምና ማስፈጸም ሲሆን የሚከተሉት ተግባራት ይገኙበታል።

1.     ሀገረ ስብከቱ በሥሩ ላሉት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የሚያስተላልፋቸው መመሪያዎች በፍጥነት ተደራሽ እንዲሆኑና ለሕዝብ ጆሮም መድረስ እንዲችሉ ማድረግ

2.    የቤተ ክርስቲያንዋን ሕግና ቀኖና ለመጠበቅና ለማስጠበቅ ይቻል ዘንድ ትምህርቶችንና መልእክቶችን እያዘጋጀ ለማስተማር

3.    የሀገረ ስብከቱንና የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትን መዋቅራዊ አሠራርን በመከተል የጋራ ተልዕኮ የሆነውን የስብከተ ወንጌል ሥርጭትን ለማቀላጠፍ

4.    የቅዱስ ሲኖዶስን መመሪያና ጥሪ በወቅቱ ለማስተላለፍ

5.    በሀገረ ስብከታችን ያለውን መንፈሳዊ እንቅስቃሴን አስመልክቶ ለምዕመናን ብርታት የሆኑ ልምዶችንና ተግዳሮቶችን ለማካፈል ድረ ገጹ ከላይ ከተዘረዘሩት ተግባራት ሌላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሀብት የሆኑ ያሬዳዊ ድርሰቶችን ያስተላልፋል። የገዳማትና የመካነ ቅዱሳን ታሪክና ሥነ ቅርስን ያስቃኛል።

በመሆኑም ትውልዱ ቅድስት ሀገሩንና እናት ቤተ ክርስቲያኑን እንዲያውቅ ታላቅ ዕድልን በመስጠት የቤተ ክርስቲያንዋ የበላይ ወሳኝ አካል የሆነውን የቅዱስ ሲኖዶስን ድምጽ ያሰማል።

ስለሆነም ሁላችሁ የዚህ ድረ ገጽ ጠቀሜታን በመረዳት ትገለገሉበት ዘንድ ጥሪያችንን እያስተላለፍን፤ መጪው ዘመን ዘመነ ማቴዎስ የሰላም፣ የፍቅር እና በመንፈሳዊ ሕይወትም የምንጎለምስበት እንዲሆን፤ ለሀገራችን ለኢትዮጵያ ሠላም ብልጽግና እና እድገትን፣ ለሕዝቧም ፍቅር እና አንድነት ያድልልን ዘንድ ዘወትር በጸሎታችን «ወይኩን ፈቃድከ » እያልን እንለምነዋለን።                

የእግዚአብሔር ፀጋ እና ረድኤት በእኛ ላይ ይደር፤ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ረድኤትና አማላጅነት ከሁላችን ጋር ይሁን !

 

 

______________________________________

አባ ዘካርያስ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
የሰሜን ምሥራቅ፣ደቡብ ምሥራቅና መካከለኛው አሜሪካ
ኒው ዮርክ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
መስከረም ፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም.