መልዕክት ከብፁዕ አቡነ ዘካርያስ፦ ጸልዩ ከመ ኢትባኡ ውስተ መንሱት


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

ጸልዩ ከመ ኢትባኡ ውስተ መንሱት

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ፦ "ይቤ እግዚእነ ዘለዘክሮተ ስሙ ሰጊድ ጸልዩ ከመ ኢትባኡ ውስተ መንሱት።" ለስም አጠራሩ ክብር፣ ምስጋና እና ስግደት ይግባውና አምላካችን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌሉ ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ (ማቴ. ፳፮፡፵፩) በማለት የጸሎትን ኃይል እንድናውቅ አስተምሮናል።

የዓለማችን ፈተና ብዙ ነውና፤ በምድርም ሳለን በተለያዩ ፈተናዎች እንፈተናለንና ዘወትር በትጋት መጸለይ እንደሚገባ ከኃጢአት በቀር እንደ እኛ የተፈተነ፤ በድካማችንም ሊራራልን የሚችል (ዕብ. ፬፡፲፭) አምላካችን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ፈተና እንዳንገባ ተግተን መጸለይ እንዳለብን አስቀድሞ ነገረን። ከሳሻችን ዲያብሎስ ዛሬም እንደ ትናንቱ የሰው ልጆችን እየፈተነ በሰላምና በፍቅር እንዳንኖር የመከራ ወጥመድን እያጠመደ እርስ በእርሳችን እንድንጠፋፋ እየፈተነን ይገኛል። የሕግ ፍጻሜው ፍቅር እርሱም ባልንጀራን እንደ ራስ መውደድ ነውና ሁላችን በፍቅር ዐይን ተያይተን ይህን ድንኳን የሚሆነውን ዓለም ትተን በእጅ ወዳልተሠራችው ልዩና ዘላለማዊ ቦታ ወደሆነችው ወደ ሰማያዊቷ ኢየሩሣሌም ለመግባት በፈተና መካከል ጽናትን የሚሰጥ አምላክን በመማጸን ልንኖር ይገባናል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ ነገር ግን እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱ ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ። (ገላ. ፭፡፲፭) ብሎ እንደጻፈልን መለያየታችንን የሚወድ የቀደመው እባብ በመከራ በሚፈትነን በዚህ ሰዓት አጥብቀን ልንጸልይ ያስፈልገናል።

እንዲህ እንደ ዛሬው ዓለም የብዙ ሚሊዮን ሕዝብ መናኽሪያ ሳትሆን ገና በመጀመርያው የሥነ ፍጥረት ዘመን ያበጃትም ይጠብቃትም ዘንድ እግዚአብሔር አምላክ የሰውን ልጅ በዔደን ገነት ሲያኖረው በቅናት በተነሣበት በጥንተ ጠላታችን ዲያቢሎስ መፈተን ጀምሯል። የሰው ልጅም በመጣበት ፈተና ሁሉ የተፈጠረበትን የቀደመ ጠባዩን እየረሳ ወንድም ከወንድሙ፣ ወገን ከወገኑ ጋር በየጊዜው እየተጋጨ በአርዓያውና በአምሳሉ የፈጠረውን አምላኩን እያሳዘነ እንደኖረ ታሪክም መጽሐፍም ይነግረናል። ፈተና ለምን መጣ ሳይሆን ከፈተና እንዴት መውጣት ያቻለናል ወደሚለው የጥበብ መንገድ ማስተዋል አርቆ አሳቢነት ነውና በሰይጣን ወጥመድ ተይዘን እንዳንቀር ለፈተናው መውጫ የሚሆነውንም መንገድ ወደሚያዘጋጀው አምላክ መጸለይ ይገባናል። ፈተና በየዘመኑ መነሣቱ ፈጽሞ አይቀሬ ነውና በልዑል እግዚአብሔር እንደ ልቤ ተብሎ የተጠራው ቅዱስ ዳዊትም በዘመኑ መከራ በጸናበት ጊዜ በጸሎት እግዚአብሔርን መማጸን ልምዱ ነውና "እማእምጥ ጸዋእኩከ እግዚኦ ስምዐኒ ጸሎትየ።" አቤቱ አንተን ከጥልቅ ጠራሁህ፤ አቤቱ ጸሎቴን ስማ። (መዝ. ፲፳፱፡፩-፪) በማለት ከባድ በሆነው መከራው መካከል መፍትሔ ለማግኘት የሚቻለው ወደ እግዚአብሔር አብዝቶ በመጸለይ በመሆኑ አቤቱ አንተን ከጥልቅ ጠራሁህ በማለት ከፈተና ወደሚያድን አምላክ እንዴት መጸለይ እንደሚገባ ነግሮናል።

ቅድስት አገራችን ኢትዮጵያም እንዲህ ያለው ውጣ ውረድ በየጊዜው ይፈትናታል። ይኼው ሰሞኑንም የተከሰተው የሰላም ችግርም ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ሕይወት እንዲጠፋ ምክንያት ሆኗል። በየጊዜው ከሚነሣ ከእንዲህ ያለው ቀውስ መላቀቅ የሚቻለው ፍጹም ሰላምን የሚያድለውን አምላካችንን በንፁህ ልቡና ሆነን ስንለምነው ነውና "በእርስዋ ሰላም ሰላም ይሆንላችኋልና ስለከተማይቱ ሰላምን ፈልጉ፥ ስለ እርስዋም ወደ እግዚአብሔር ጸልዩ" እንዳለ ሁላችንም በአንድነት ሆነን እግዚአብሔር አምላካችን ለአገራችን ለኢትዮጵያ ፍጹም ሰላምን ይሰጥልን ዘንድ በተለይም በዚህ በሱባዔ ወቅት አጥብቀን እንድለምነው አባታዊ መልእክቴን አስተላልፋለሁ።

ለችግር መፍትኄን፣ ለአገርና ለሕዝብም ፍጹም ሰላምን የሚሰጥ እግዚአብሔርን ካልያዙ ጠዋት የተማመኑበት ሰላምና ደስታ ማታ እንደ ጤዛ ተኖ ሌላ ድካምና መከራ በሰው ልጅ ሕይወት ላይ ይተካል። አምላኩን የያዘ ሕዝብ ግን ሁልጊዜም "በልቤ ደስታን ጨመርህ፤ ከስንዴ ፍሬና ከወይን ከዘይትም ይልቅ በዛ። በሰላም እተኛለሁ አንቀላፋለሁም፤ አቤቱ፥ አንተ ብቻህን በእምነት አሳድረኸኛልና።" (መዝ. ፬፡፰) እያለ ይኖራል። እኛም እምነታችን በእግዚአብሔር የጸና ነውና አበው ሳያንቀላፉ ከዓመት እስከ ዓመት ቅዱስ! ቅዱስ! ቅዱስ! የሠራዊት ጌታ ልዑል እግዚአብሔር ቅድስት አገራችንን እና ሃይማኖታችንን ጠብቅልን በማለት የሚማጸኑትን ተማጽኖ በመማጸን ጸሎትን ወደሚሰማ ወደ ልዑል እግዚአብሔር ልንለምን ይገባናል።  

አገራችን ኢትዮጵያንና ሃይማኖታቸው የቀና የአባቶቻችንን አብያተ ክርስቲያናትንም ሁሉ እግዚአብሔርንም በማመን በውስጡ የሚኖሩትንም ሁሉ ጠብቅልን (ቅዳሴ ባስልዮስ ቁጥር ፶፮) በማለት ዘወትር በማይቋረጥ የቅዳሴ ጸሎት የምታመሰግን አገራችንን ልዑል እግዚአብሔር በበረከት ይጎብኝልን። መጽሐፍ እግዚአብሔርን በመፍራት በጸሎትና ምስጋና ለትውልድ ለወገን ለአገራችሁ ሰላምን ፈልጉ እንደሚለው ሃይማኖታችን ተጠብቆ እንዲኖር ካህናት ፣ መምህራነ ወንጌል፣ ዲያቆናትና ማኅበረ ምእመናን በሙሉ ፍጹም ጸሎት በማቅረብ ሁሉን ማድረግ ወደሚቻለው አምላክ ጩኸታችሁን አሰሙ። እንደ ቃላችን ሊያከናውንልን የታመነ አምላክ ነውና አባቶቻችን ጸልየው የጸሎታቸውን መልስ እንዳገኙት እኛም እንደ አባቶቻችንን በመጸለይ ለአገራችን ፍጹም ሰላምን እንዲሰጥልን በየአብያተ ክርስቲያኑ የምትገኙ የእግዚአብሔር ልጆች ልመናችሁን አቅርቡ። የነነዌ ሕዝብ ከመጣበት ፈተና መዳን የቻለው ጸሎትን የሚሰማ አምላክ የአረጋውያኑን፣ የነገሥታቱን፣ የወጣቱንና የሕፃናቱን ፆም ጸሎት ሰምቶ በመሆኑ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለሱባዔ በምትቆሙበት ቦታ ከሕፃን እስከ ዓዋቂ ሁላችሁም ወደ እግዚአብሔር እንድትማጸኑ በድጋሚ አባታዊ መልእክቴን አስተላልፋለሁ።

የልዑል እግዚአብሔር ቸርነት፣ የእግዚአብሔር ወልድ ፍቅር፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አንድነት ዘወትር አምላኳን ከምትወድና ከምታከብር ከአገራችን ከኢትዮጵያ ጋር ይሁን። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በጸሎትዋ፣ ጻድቃን ሰማዕታት በምልጃቸውና በተሰጣቸው ቃል ኪዳን ምድራችንን የሰላም ምድር ያድርጉልን። አሜን!

እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን፤ የቅድስት ድንግል ማርያም ረድኤት አይለያችሁ!