ሊቀ መዘምራን ዲያቆን ቴዎድሮስ ዮሴፍም እና ቀሲስ አንዱዓለም ዳግማዊን ይመለከታል

በቦስተን እና አካባቢው ላላችሁ የኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን
ካህናት፣ ዲያቆናት፣ ምእመናን እና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች

ከዚህ ቀደም ብለን በቁጥር 136/2016 January 27, 2016 በተጻፈ ደብዳቤ እንዳሳወቅነው ቅዱስ ሲኖዶስ እና ሀገረ ስብከቱ ሳይፈቅድ ሊቀ ጉባኤ ኤርምያስ በቦስተን ከተማ «ደብረ ብርሃን ሥላሴ» ብለው ቤተ ክርስቲያን አቋቁሜአለሁ በማለታቸው ሥልጣነ ክህነታቸው ሙሉ በሙሉ መታገዱን ማሳዎቃችን ይታወሳል። በዚህም ተግባራቸው ለሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ያላቸውን ንቀት ከማሳየታቸውም በላይ የቦስተን ምእመናን የጥርና የሐምሌ ሥላሴ እየመጡ የሚሳለሙትን፣ ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን ጀምሮ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ፣ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ልዩ ትኩረት የተሰጠውን እና መንበረ ጵጵስና የሆነውን የኒውዮርክ ደብረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያንን ተገዳድረዋል።

ሥልጣነ ክህነታቸው ከታገደ በኋላም ለተለያዩ ካህናት የአገልግሎት ግብዣ ጥሪ ሲያቀርቡ «ሥልጣነ ክህነትዎ ስለታገደ አብረንዎት አናገለግልም» በመባላቸው ምክንያት አሁን ደግሞ ፊታቸውን በስደተኛው ክፍል እናገለግላለን ወደሚሉ ካህናት በማዞር መጋቢት ፪ እና ፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. ከስደተኛው ክፍል ቀሲስ አንዱዓለም ዳግማዊን እና በቅርቡ ከኢትዮጵያ የመጣውን ሊቀ መዘምራን ዲያቆን ቴዎድሮስ ዮሴፍን በመጋበዝ ጉባኤ በማዘጋጀት ምእመናንን ማደናገሩን ቀጥለውበታል።

ቀሲስ አንዱዓለም ዳግማዊ ዛሬ አሜሪካ መጥቶ ስደተኛውን ክፍል ከመቀላቀሉ በፊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ክህነት ሰጥታ፣ ከአሏት መንፈሳዊ ተቋሞቿም ዋነኛ በሆነው በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አስተምራ እና መምህር ብላ ማዕረግ ሰጥታ ለክብር አብቅታዋለች። ሊተገብረው ዳገት በሆነበት የሕግ መጽሐፍ ላይ «ያለ ሊቀ ጳጳስ የምትኖር ቤተ ክርስቲያን እንደ ፈት ናት» የሚለውን የተማረው ቀሲስ አንዱዓለም እኔ ከስደተኛው ወገን ስለሆንኩ ማንም አይነካኝም በሚል የሰነፍ አስተሳሰብ ሥልጣነ ክህነቱ ከታገደ ጋር በአገልግሎት መተባበርን እንደመረጠ እንረዳለን። ሆኖም ግን እርሱ አክብሮ አይያዘው እንጂ ሥልጣነ ክህነቱን የተቀበለው ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃነ ጳጳሳት ስለሆነ ይህንንም ክህነት የማገዱ ሥልጣን አሁንም ቢሆን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃነ ጳጳሳት ነው። ከስደተኛው ወገን ነው በሚል ቸላ ሳንል በዚህ የድፍረት ተግባር እንዳይተባበር ብንመክረውና ብናዝዘውም እምቢ ብሎ የሊቀ ጳጳሱን ትዕዛዝ በመተላለፉ ምክንያት ከዛሬ ጀምሮ ሥልጣነ ክህነቱን ሙሉ ለሙሉ አግደናል።  ሊቀ መዘምራን ዲያቆን ቴዎድሮስ ዮሴፍም ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ከጣሱ እና ከተወገዙ ካህናት ጋር በመተባበር ቤተ ክርስቲያንን እንዳይበድል በተደጋጋሚ ያሳሰብነውን፣ የመከርነውን እና ያዘዝነውን አቃልሎ ከተወገዙ ካህን ጋር በአገልግሎት በመተባባሩ ከዛሬ ጀምሮ ሥልጣነ ክህነቱን አግደናል። በዚህ ጥፋቱ ተጸጽቶ ይቅርታ የሚጠይቅ ከሆነ ወደፊት የሚታይለት ይሆናል።