ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ የሊቀ መዘምራን ዲያቆን ቴዎድሮስ ዮሴፍን ይቅርታ ተቀብለው አስተላልፈውበት የነበረውን እገዳ አነሡለት

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰሜን ምሥራቅ፣ ደቡብ ምሥራቅና መካከለኛው አሜሪካ የኒውዮርክ ሀገረ ስብከት Ethiopian Orthodox Tewahedo Church, New York Archdiocese

የተወደዳችሁ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናት፣ ዲያቆናት፣ ምእመናን እና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች፤

 

ጉዳዩ፦ በሊቀ መዘምራን ዲያቆን ቴዎድሮስ ዮሴፍ ላይ አስተላልፈነው የነበረውን እገዳ ማንሳታችንን ስለማሳወቅ

«ኵሉ ተግሣጽ ኢይመስል ትፍሥሒተ በጊዜሁ። ዳዕሙ ኀዘን ውእቱ ወድኅረሰ ትፈርይ ሰላመ ለእለ ተገሠጹ - ተግሣጽ ምክር ለጊዜው ደስ አያሰኝም የሚያሳዝን የሚያስከፋ ይመስላል እንጂ። ኋላ ግን ታግሠው ለተቀበሏት ሰዎች ከእግዚአብሔር ዘንድ አንድነትን ሰላምን ታመጣላቸዋለች። ወተዐስዮሙ ጽድቀ - መልካም ዋጋቸውንም ትሠጣቸዋለች።» ዕብ ፲፪ ፣ ፲፩-፲፪

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ለምታከናውናቸው ማንኛውም ተግባሮቿ ሁሉ ሥርዓት ያላት እና ለዚህ ሥርዓቷም ጠባቂ እና አስከባሪ አካል ያላት መንፈሳዊት ተቋም ናት። በሀገር ውስጥም ሆነ በተለይም ደግሞ በውጪው ዓለም የምንገኝ የተዋሕዶ ልጆች የሃይማኖታችንን ስም እና ማንነት በኩራት ልንናገር የበቃነው አባቶቻችን ለሠሩት ሥርዓት ተገዢ የሆኑ አያት ቅድመ አያቶች ስለነበሩን እና ይህንንም ሥርዓት ለማስፈጸም የተጣለባቸውን ኃላፊነት ቁም ነገር ብለው የያዙና የተጉ አባቶች ስለነበሩን ብቻ ነው።

ሠልጥኛለሁ በሚለው በምዕራቡ ዓለም ስለምንኖር ብቻ በሥርዓት ወልዳ እና አሳድጋ ለክብር ያበቃችንን ቤተ ክርስቲያንን መዳፈር፣ ብዙ ተከታይና አድናቂ አለኝ በሚል ብቻ ሥርዓቷን መናቅ እና ማቃለል ክብርን ሳይሆን ወቀሳን እና ተግሣጽን የሚያስከትል ይሆናል። ይህን የቤተ ክርስቲያንን ሕግ እና ሥርዓት ለማስከበር ከቅዱስ ሲኖዶስ የተጣለብንን ኃላፊነት የተሸከምን ሁላችን - እኔም ሆንኩ በእኔ ማዕረግ ያሉ ሁሉ «ሰው ቅር እንዳይለው» በሚል ፈሊጥ ብቻ እግዚአብሔር እንደሚያዝዘው እና ሕገ ቤተ ክርስቲያን እንደሚደነግገው ሳይሆን ሕዝቡን ደስ የሚያሰኘውን ብቻ በመሥራት ከሰው ጋር ተመሳስሎ እና አፍአዊ መወደድን ይዞ መኖርን የመረጥን ጊዜ ያን ጊዜ በብዙ መስዋዕትነት ከእኛ ዘመን የደረሰችዋ ቤተ ክርስቲያን መልኳ እና ቅርጿ እንዲጠፋ ካደረጉት መካከል ተደምሮ መመዝገብን እና መወቀስን ያመጣብናል።

ይህንንም ጠንቅቀን በመረዳት እና ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ ለሰው ፊት ሳናደላ ሥርዓቷን የተጋፋውን ሁሉ ወደ ሥርዓቷ እንዲመለስ እያደረግን እንገኛለን።

-       በዚህም የተነሳ ነው በሀገረ ስብከታችን ጣልቃ በመግባት በሚኒያፖሊስ በሚገኘው በተወገዘ ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ከተወገዘ ካህን ጋር በአገልግሎት ተሳትፈው፣ የአዲስ ቤተ ክርስቲያን መሠረትም በማስቀመጥ እና ሥልጣነ ክህነት በመስጠት ሕገ ቤተ ክርስቲያንን የጣሱትን ብፁዕ አቡነ ዳንኤልን ተግባራቸውን አውግዘን ቅዱስ ሲኖዶስ እርምጃ እንዲወስድ ያስደረግነው ። 

-       በዚህም የተነሳ ነው አለን በሚሉት የተከታይ ብዛት ምክር መስማት ተስኗቸው በተወገዘ ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ከተወገዘ ካህን ጋር አብረው በማገልገል ቤተ ክርስቲያንን ደጋግመው የበደሉ እነ መምህር ምሕረተአብ አሰፋ እና መጋቤ ሐዲስ እሸቱ ዓለማየሁ በሀገረ ስብከታችን እንዳያገለግሉ ያገድናቸው፤

-       በዚህም የተነሳም ነው ባሳለፍነው ሳምንት በቦስተን ከተማ በሚገኝና በተወገዘ ካህን እተዳደራለሁ በሚል ቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ላይ በመሳተፍ የቤተ ክርስቲያንን ሕጓን እና ሥርዓቷን በተጋፉት ላይ ሀገረ ስብከታችን የቤተ ክርስቲያን ሕግ በሚያዝዘው እና በሚፈቅደው መሠረት የእርምት እርምጃ ወስዶ የነበረው።

ጥፋት ከመፈጸማቸው በፊት ምክራችንን ተቀብለው ከጥፋት የታቀቡ፣ ካጠፉም በኋላ በጥፋታቸው ተጸጽተው የተመለሱ የመኖራቸውን ያህል ባጠፉት ጥፋት ሥልጣነ ክህነታቸው የተያዘባቸው አንዳንዶችም «አጥፍቻለሁና ይቅር በሉኝ» ማለትን በዐውደ ምሕረት ማስተማር እንጅ መተግበር ተስኗቸውና ይቅርታ መጠየቅ ዳገት ሆኖባቸው እስከአሁን ድረስ ሥልጣነ ክህነታቸው እንደተያዘባቸው የሚገኙም አሉ። ከእነዚህም መካከል ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አስተዳደር ውጪ በመሆን በገለልተኛ አስተዳደር የራሱን ቤተ ክርስቲያን ከፍቶ ሥርዓት አልበኛነትን ምእመኑ እንዲለማመደውና እንደ ነውርም እንዳይቆጥረው በማድረግ ቤተ ክርስቲያንን በእጅጉ እየበደላት በሚገኘው በቀሲስ ዘበነ ለማ ጉያ ሥር ተደብቆ የይቅርታ ደብዳቤ እልካለሁ እያለ መልእክተኛ በመላክ በዚያው የውኃ ሽታ ሆኖ የቀረው እና ሕገ ቤተ ክርስቲያንን በመተላለፉ ሥልጣነ ክህነቱ የተያዘበት «ቀሲስ» ነህምያ ጌጡ አንዱ ነው።

ልጃችን ሊቀ መዘምራን ዲያቆን ቴዎድሮስ ዮሴፍ ለአገረ አሜሪካ እንግዳ በመሆኑና በነበረበት ውጫዊ ተፅዕኖ ምክንያት በውጪው ዓለም ፈተና የሆነብንን ሥርዓተ አልበኝነትን በጥልቅ ባለመረዳት ቦስተን ከተማ በሚገኘው እና የተወገዘ ካህን «ደብረ ብርሃን ሥላሴ» ብሎ ከሥርዓት ውጭ በመመሥረት አስተዳድረዋለሁ በሚለው ቤተ ክርስቲያን ተገኝቶ በማገልገሉ ሥልጣነ ክህነቱን ለጊዜው ማገዳችን ይታወሳል። ተግሣጽን ለመቀበል ፍጹም የተዘጋጀ ልቡና ያለው ይህ ልጃችን ሊቀ መዘምራን ዲያቆን ቴዎድሮስም ይህንን ተግሣጽ አክብሮ እና ዋጋ የሚያሰጥ መሆኑንንም ተረድቶ ሳይውል ሳያድር ከእኔ ከክፍሉ ሊቀ ጳጳስ ጋር በመነጋገር ለአጠፋው ጥፋትም ፍጹም ልባዊ የሆነ ይቅርታ ጠይቋል፤ ይህም የልጃችንን መንፈሳዊ ብስለት እና ለአባቶች ያለውን ክብር በጉልህ ያሳያል።

በግዕዝ ቴዎድሮስ በላቲን ቴዎዶ(ር)

ከተኩላዎች ሰፈር መጠሪያው ወልጋዶ፣

ምንም ሳይረዳው በድንገቱ ሄዶ፣

በተግሣጽ ጠራቺው ቅድስት ተዋሕዶ።

እንዲህም አለቺው ወይ ነዶ ወይ ነዶ!

እንዴትስ ብለህ ሄድህ … እውነት ልብህ ፈቅዶ?

መች ተለመደና ከተኩላ ተዛምዶ።

በልጃችን በሊቀ መዘምራን ዲያቆን ቴዎድሮስ ዮሴፍ ላይ ያስተላለፍነው ጊዜያዊ እገዳ እንጂ ውግዘት አለመሆኑን ባለመረዳት «ተወግዘሃል» ባሉት ሰዎች መንፈሱ እንደተጎዳ እንረዳለን። የጥፋቱን ልክ በመመዘን እና ከጥፋቱም ተጸጽቶ የሚመለስ ልጃችን እንደሆነ ስላመንን በብዙ ተጋድሎ ያስከበርነው ሀገረ ስብከታችን በእንግድነቱና ባለማወቁ ምክንያት በፈጸመው ስህተት በሚከፈት ቀዳዳ ሌሎችም ገብተው እንዳይቦርቁበት በማሰብ ያስተላለፍንበት ጊዚያዊ እገዳ ብቻ እንጂ ውግዘት አልነበረም።

በመሆኑም ልጃችን ሊቀ መዘምራን ዲያቆን ቴዎድሮስ ዮሴፍ ባጠፋው ጥፋት ፍጹም በመጸጸት፣ የባልንጀሮቹን ምክር በመስማት እንደ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ከእኔ ከክፍሉ ሊቀ ጳጳስ ጋር በፍጹም ትኅትና በመነጋገር ይቅርታን ስለጠየቀ በቁጥር 144/2009 መጋቢት 1 ቀን 2009 ዓ.ም. አስተላልፍነው የነበረውን የሥልጣነ ክህነት እገዳ ሙሉ ለሙሉ አንሥተን ከቅድስተ ቅዱሳኑ ጀምሮ ባለው የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት በሙሉ በነበረው ክብር ያገለግል ዘንድ ከታላቅ ክብር ጋር እግዱን ያነሳንለት መሆኑን እናሳውቃለን። አንተን ልጃችንንም ይህንን ተግሣጽ ተቀብለህ በመመለስህ ቤተ ክርስቲያን ታመሰግንሃለች። ሊቀ መዘምራን ዲያቆን ቴዎድሮስ ዮሴፍ ዛሬም ይሁን ወደፊት ወደ ሀገረ ስብከታችን በሚመጣበት ጊዜ በሀገረ ስብከታችን በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንዲያገለግል የፈቀድንለት መሆናችንንም ጨምረን እናሳውቃለን።

እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክ