ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል፣ ኢንዲያናፖሊስ

የደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ በኢንዲያናፖሊስ ከተማ በቅዱስ ሚካኤል ፅዋ ስም ይሠባሰቡ በነበሩ የቤተ ክርስቲያን ልጆች አማካኝነት የተጀመረው እንቅስቃሴ አድጎ በወቅቱ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሃገረ ስብከት ሊቀ ዻዻስ በነበሩት ብፁዕ አቡነ ማትያስ (አሁን ፓትሪያርክ) መልካም ፈቃድ ስርዓቱ በሚያዘው መሠረት ቆሞስ አባ /ማሪያም አስተዳዳሪና አገልጋይ ካህን ሆነው በምደባ ከታቦተ ቅዱስ ሚካኤል ጋር መጥተው ጥር ፲፫ ቀን ፲፱፻፺፪ ዓ.ም. በሃገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ቡራኬ በይፋ ተመሠረተች።

የቤተ ክርስቲያኗ አገልግሎት የተጀመረው በተውሶ በተገኘ ቦታ ላይ ድንኳን በመዘርጋት ሲሆን በቀጣይ ከአንድ ፈነራል ቤት (Funeral Home) ወደ ሌላ በመሄድ ለ፭ ዓመታት በፈታኝ ሁኔታ ሊቀጥል ችሏል። ከዚያም በእግዚአብሔር ፈቃድ በመልአከ ሰላም ቆሞስ አባ ኃይለ ማርያም አስተባባሪነት ፣ በደብሩ አስተዳደር ኮሚቴና ምእመናን ከፍተኛ ጥረት በ 939 S. DIVISION ST. የሚገኘው ሕንጻ ግዢ ሕዳር ፲፪ ቀን ፲፱፻፺፯ ዓ.ም ተፈጸመ። የዚህ ሕንጻ ቅዳሴ ቤት በዓልም የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማትያስ (አሁን ፓትሪያርክ) በተገኙበት ጥር ፲፫ ቀን ፲፱፻፺፯ ዓ.ም በደማቅ ሥነ ሥርዓት ተከብሯል።

በዚህ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ለ፰ ዓመታት አገልግሎቱ ሲካሄድ ቆይቶ የምእመናኑ ብዛት ከሕንጻው አቅም በላይ እየሆነ በመምጣቱ ትልቅ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ለመግዛት እንቅስቃሴ ተጀመረ። ከብዙ ፍለጋ በኋላ ስንገለገልበት ከነበረው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን አጠገብ የነበረ ሕንጻ እንደሚሸጥ በመታወቁ በእግዚአብሔር ፈቃድ በቅዱስ ሚካኤል አማላጅነት አሁን የምንገለገልበትን ታላቅ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በመግዛት ከቀድሞው ቦታ ጋር ተጨምሮ የሰፊ ይዞታ ባለቤቶች ለመሆን ችለናል። ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑም በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት ከተስተካከለ በኋላ ጥር ፳፭ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም. በሃገረ ስብከታችን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ ተባርኮ አገልግሎቱ በሰፊው ቀጥሏል።

በአንድ ካህን የተጀመረው አገልግሎት አድጎ ዛሬ በሙሉ ልዑካን የሚቀደስበት ፣ የጥምቀት ፣የተክሊል ፣የፍታት ወዘተ. አገልግሎት በተሟላ ሁኔታ የሚፈጸምበት ፤ ስብከተ ወንጌልም ዘወትር እሁድ ፣ በወርሃዊ ጉባኤ እንዲሁም በዓመት ፬ ጊዜ በተጋበዙ መምህራነ ወንጌል በስፋት የሚሰጥበት በመቶዎች ለሚቆጠሩ ምእመናን መጽናኛ ታላቅ ደብር ሆኗል። በተጨማሪም ረጅም እድሜ ያስቆጥረው የደብሩ ሰንበት ትምህርት ቤት በመዝሙር ፣ በልማት በመሳሰሉት መስኮች ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ በተጨማሪ  ሕጻናትን በየእድሜያቸው በመመደብ የፊደል ፣ የመዝሙርና የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በመስጠት ተተኪ ለማፍራት ከፍተኛ ሥራ በማከናወን ላይ ይገኛል።

በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያናችን ላለፉት ፲፮ ዓመታት ብዙ ፈተናዎችን ተቋቁማ ፣ አንድነቷን ጠብቃ እዚህ እንድትደርስ ያደረጋት የእግዚአብሔር ቸርነት የቅዱስ ሚካኤል አማላጅነት ሲሆን  በየዘመኑ በሀገረ ስብከቱ የተመደቡት ብፁአን አባቶች (የብጹእ አቡነ ማትያስ ( ኣሁን ፓትርያርክ) ፣ የብጹእ አቡነ  አብርሃም እንዲሁም በአሁኑ  ሰዓት የሀገረ ስብከታችን ሊቀ ጳጳስ የሆኑት የብፁዕ አቡነ ዘካርያስ) ቡራኬና ጸሎት ፣ የደብሩ አስተዳዳሪ የመልአከ ሰላም አባ ኃይለ ማርያም ትጋት ፣ እንዲሁም የካህናቱ ፣ የዲያቆናቱ ፣ የሰበካ ጉባኤው፣ የሰንበት ትምህርት ቤቱና የምእመናኑ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠው ነው።