ወርቃችንን አንጥልም

ነገሩ ሆነና ቅዳሴው ሲያልቅበት፣
ዝም እንዳይል አፉ ቀረርቶ ሞላበት።
አሁን በእኛ ዘመን ትምህርቱ አነሰና፣
በአዋጅ ተነገረ ኦርጋን እንዲጠና።
እውነት ይኼ ነው ወይ ያለው አስተምህሮ፣
በኦርጋን አመስግን አስወግድ ከበሮ።
ገና ጉድ ይሰማል ጆሮ አይሰማው የለ፣
ይኽ የአባቶቻችሁ ትዕዛዝ ነው ተባለ።
አደራ ተቀባይ ዋናው ተሐድሶ፣
ዜናውን አብራርቶ አሰማን መልሶ። 
በልቡ ስላለ በኦርጋን መጫወት፣
ጥቅስ ይጠቅስ ጀመር ሊለን "ምን አለበት"።
እንኳንስ ዘንቦብህ እንዲያውም ጤዛ ነህ፣
አፈፍ አደረግኽው ቃሉን ቶሎ ብለህ።
ይኼ ጥናት ነው ወይ አጥንተህ ሞተኻል፣
ጉግል ሰርች አድርጉ ብለህ ጠቁመኻል።
ለግብፅ ፒያኖ ለሶርያ ኦርጋን፣
ይዘው ቢደምቁበት እኛ ምን አገባን።
ማመስገኛ ዜማ ኢትዮጵያ ግን አላት፣
አምላክ የመረጠው ያሬድ ያህል አባት።
በአባታችን በኩል ለእኛ ከተሰጠን፣
ዛሬም ወደፊትም እንጠብቀዋለን።
ብዙዎች ኢትዮጵያን በዚህ ምስጋናዋ፣
ዕፁብ ድንቅ ይሏታል በመዝሙር ዕሴትዋ።
ኋላ ቀር ሆናለች ከመስመሩ ወጥታ፣ 
ፒያኖ የማታውቅ ኦርጋን የማትመታ።
ያሉት የእኛው ናቸው እኛ የምናውቃቸው፣
በእጃቸው ያለው ወርቅ መዳብ ሆኖባቸው።
ኦርጋን ቦታ ፈልግ ፒያኖ ተመለስ፣
ዳንኪራ ቤት እንጂ አትገባም መቅደስ።
ከካሊፎርንያ ከዴንቨር ሆናችሁ፣
ፒያኖ ቫዮሊን ኦርጋን እያላችሁ፣
ምሥጢር ላይወጣበት ብታመሰጥሩ፣
የእናንተን ትታችሁ ለሌላ ብታድሩ፣
እኛ ግን እኛ ነን ባለን እንገናለን፣
በያሬድ ውብ ዜማ እንዘምራለን።
አንተ ሞኝ ለእራስህ በቫዮሊን ግነን፣
በጊታር ስትዘምር ስትዘል እናውቃለን።
ማስረጃ አንፈልግም ግብፅ ግብፅ አትበለን፣
ኖረን አይተነዋል ሁሉን እናውቃለን።
ትናንት ፓስተር ሆነህ ዛሬ የተካንከው፣
መልሰህ በጊታር ልትዘምርብን ነው።
ይቺን ጫፍ ስታገኝ የተደሰትክበት፣
ልብህ ስላለ ነው የጥንቱ ማንነት።
የካሊፎርንያው የዴንቨሩም ወንድም፣
ከንቱ ደከማችሁ ላያምናችሁ ማንም።
ከአገር ጫፍ አገር ጫፍ የኢትዮጵያ ሕዝብማ፣
ከበሮውን ይዞ ሲዘምር ተሰማ።
አላያችሁም ወይ የትናንቱን ጥምቀት፣
አምሮ ደምቆ ሲታይ ኦርጋን ሳይገባበት።
አታስቁን ይብቃ አገር ስትቀይሩ፣
ሃይማኖት መለወጥ ላይሆን አትሞክሩ።
ዝም ካላላችሁ እንመለሳለን፣
አሁን በዚህ ይብቃ ለጊዜው ይቆየን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
 

አብርሃም ሰሎሞን።
ጥር ፲፪/፳፻፰ ዓ.ም.