ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ ከኒውዮርክና አካባባቢው ጋር ደርበው ምዕራብ ጎጃም ፍኖተ ሰላም ሀገረ ስብከትን እንዲያስተዳድሩ ቅዱስ ሲኖዶስ ወሰነ

የኒውዮርክ ሀገረ ስብከት ሰፊና ብዙ ታሪክ ያለው በመሆኑ በዚህች አጭር መልዕክት ሁሉንም መጥቀስ ስለማይቻል ዋናዋውን ብቻ እንጠቅሰዋለን፦

የኒውዮርክን ሀገረ ስብከት የማቋቋም ሥራ የተጀመረው እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ 1937 ማለትም ጣልያን ኢትዮጵያን ከወረረበት ጊዜ አንስቶ ነው። ከ 1937 እስከ 1952 ባለው ጊዜም ይህ ይዞታችን በቤተ ክርስቲያን ግንኙነት ብቻ ሳይሆን በአገር ደረጃ በተለይም በግርማቂ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ጋር በመመካከር ለመጀመሪያ ጊዜ በ1952 አባ ገብረ ኢየሱስ መሸሻ (በኋላ ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ የሆኑትን አባት) አስፈላጊ የሆኑትን ንዋየ ቅዱሳትና የአጋዕዝት ዓለም ሥላሴን ታቦት ይዘው ወደ Bronx, New York ገብተው አገልግሎት እንዲጀምሩ ተደረገ። እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁንና ይህም ማለት ከቅድስት አገር ኢየሩሳሌም ቀጥሎ ከኢትዮጵያ ውጭ የኒውዮርክ ሀገረ ስብከት በሁለተኛ ደረጃ ራሱን የቻለ ጽ/ቤትና መንበረ ጵጵስና ያለው ሆኖ አቅሙ በፈቀደ መጠን ምዕራቡን ክፍለ ዓለም ሲያገለግል የቆየ ነው

ለመጀመሪያ ጊዜ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ (በሁዋላ ሰማዕቱ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ) የሐረር ሊቀ ጳጳስና የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ረዳት ነበሩና በቅዱስነታቸው መልካም ፈቃድ በ 1954 ዓ.ም. ሀገረ ስብከቱን እና ቤተ ክርስቲያኑን ለመጎብኘትና ለማጠናከር መጡ። በዚያን ጊዜ ብፁዕነታቸው 275 የዚህ አገር ተወላጆችን እንዳጠመቁ ታሪክ ይመሰክራል። በኋላም በ 1959 ዓ.ም. ብፁዕነታቸው መጥተው ብዙ ምእመናንን አስተምረውና አጥምቀው ተመልሰዋል።

ለመጀመሪያ ጊዜ በጳጳስ ደረጃ ቤተ ክርስቲያኑን እና ሀገረ ስብከቱን ለማቋቋም የተላኩት ታላቁ አባት አባ ገብረ ኢየሱስ አገሩን አውቀውታል ቋንቋውንም በሚገባ አቀላጥፈው ስለሚችሉ ከእርስዎ የተሻለ የለም በማለት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ተሹመው መጥተው በተለይም በጃማይካና በዚያ አካባቢ የሚገኙ ደሴቶች ብዙ ሕዝብ በማጥመቅ በርካታ አብያተ ክርስቲያናትንም ተክለዋል።

በ 1962 ዓም ደግሞ አባ ላዕከ ማርያም ማንደፍሮ (በበኋላ ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ የሆኑት) እያገዟዋቸው በፊት ከነበረው በላይ አንድ ላይ ሆነው ብዙ ሥራ ሠርተዋል። በ 1979ም ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ በእድሜ መግፋት ምክንያት ወደ አገራቸው ሲገቡ በእርሳቸው እግር ተተክተው ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ ለበርካታ ዓመታት አገልግለዋል።

ከብፁዕ አቡነ ይስሐቅ በኋላ ደግሞ የአሁኑ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የ North America and Canada ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ሀገረ ስብከቱን አስተዳድረዋል። ከዚያም በሁዋላ በምዕራቡ ክፍለ ዓለም የምእመናን እና የአብያተ ክርስቲያናት ቁጥር እየጨመረ ስለመጣ አስቀድሞ አንድ ሀገረ ስብከት የነበረው የዲሲ፣ የካሊፎርኒያ፣  እና የኒውዮርክ ሀገረ ስብከት ተብሎ በሦስት አኅጉረ ስብከቶች ሲዋቀር ይህንን ለማሸጋሸግ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲቀየሩ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ወደ ኒውዮርክ ተመደቡ። ብፁዕ አቡነ አብርሃም ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ መልካም ፈቃድና በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ ወደ ኒውዮርክ ተመድበው በመምጣት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የኒውዮርክ ሀገረ ስብከትን ላለፉት አሥር ዓመታት እያስተዳደሩ ይገኛሉ።

 

lm.PNG
abunezekarias.PNG