ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ ለሊቀ ጉባኤ ኤርምያስ ወልደ ኢየሱስ የሰጧቸውን ቀኖናዊ ቅጣት ሲጨርሱ የያዙባቸውን ሥልጣነ ክህነት እንደሚያነሱላቸው አስታወቁ፣ የቋሚ ሲኖዶስ የቅርብ ጊዜ አካሄዶች ወደ አንቀጽ 32 እንዳያመራን ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳሰቡ

ለሊቀ ጉባኤ ኤርምያስ ወልደ ኢየሱስ
ባሉበት

በቁጥር 10/2010  የካቲት 10/2010 የጻፉት ደብዳቤ ደርሶኝ በጥሞና ተመልክቸዋለሁ። በአሜሪካ አገር በቦስተን ከተማ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጪ የከፈቱት የሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ያለአግባብ በመሆኑ ከሥልጣነ ክህነት መታገድዎ ይታወሳል።

የታገዱበትም ምክንያት የሚከተለውን በመሻርዎ ነው፦

ባስ 94 «ወኢይሕንፁ ቤተ ክርስቲያን ዘእንበለ በትዕዛዘ ኤጲስ ቆጶስ» ባስልዮስ በ 94ኛው አንቀፅ «ያለ ኤጲስ ቆጶሱ አንድም ያለ መጽሐፍ ትዕዛዝ ቤተ ክርስቲያን አይሥሩ»

«ወለ እመ ታሀበለ ፩ሂ ወገብረ ካልኣ እምዝንቱ ኢይቅረብ ቁርባነ ውስቴታ እስከ ለዓለም - ከኤጲስ ቆጶስ ፈቃድ አንድም ከመጽሐፍ ትዕዛዝ ወጥቶ አንዱ ቢሠራ ለዘለዓለሙ አይቁረብባት፤ አንድም ኢይትቄረብ ይላል - ለዘለዓለሙ አይቆረብባት እንደ ገበያ እንደ በረት ፈት ሁና ትኑር » «ወለ እመ ተኅበለ ካህን ዘንተ ወቀርበ በውስቴታ ቁርባነ ይትመተር - ካህን ደፍሮ ቢሰዋ ቢቆርብባት ከሹመቱ ይሻር» ስለሚል እርስዎም ከሥልጣነ ክህነት ታግደው የቆዩበት ይህ ነው።

ይህም ቀኖናዊ ሕግ የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም ከጠዋቱ 4:30 ላይ እኔም ባለሁበት ወደ ቋሚ ሲኖዶስ ቀርቦ የቀኖና አተረጓጎም ከተሰጠበት በኋላ ይህ ጉዳይ እንደ ሕጉ (ከታች ያለውን ትንታኔ ይመልከቱ) መታየት ያለበት በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ እንደሆነ ታምኖበት ቋሚ ሲኖዶሱ አመራር በመስጠት ወደ እኔ መርቶታል። በዚህም መሠረት እርስዎም የክህነት እገዳ ይነሣልኝ ጥያቄ ጽሑፍ ወደ እኔ ወደ ሊቀ ጳጳሱ ጽፈዋል።

መጻፍ የነበረብዎት ስለእራስዎ ብቻ መሆን ሲገባ ከእናት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ያልሆኑትን መሪጌታ ፀሐይ ብርሃኑን እና ሊቀ ሊቃውንት «ቆሞስ» አባ ወርቅነህ ኃይሌን ጠቅሰዋል፣ «ቆሞስ»ም ብለዋቸዋል። በመሠረቱ ቆሞሳት አይደሉም! በሕግ የነበሩ ካህን ናቸው እንጂ። ቆሞስ ማለትም በድንግልና የመነኮሰ፣ ወደ ኤጲስ ቆጶስነት ሊሸጋገር የሚችል ማለት ነው።  «ቆሞስ ብሂል መትልወ ኤጲስ ቆጶስ» ተብሎ እንደተጻፈ።

በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀፅ 35 ቁጥር 1 በፊደል ለ እንደተደነገገው በመቀጠልም እርስዎ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን በመጣስ ቅዱስ ሲኖዶስ ያልወሰነውንና ያላወቀውን «ማሳቹሴትስ ሀገረ ስብከት» ብለውም ማኅተም አስቀርጸዋል። በሕግ ያልተፈቀደውን ቤተ ክርስቲያንም «ደብረ ብርሃን» ብለው ሰይመዋል። ታቦቱንም በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ሳይባረክና በቅብዓ ሜሮን ሳይታተም አስገብተዋል። ይህ ሁሉ የቀኖና ሽረትና ስብረት ነው!

ከዚህም ሌላ በጻፉት ደብዳቤ ላይ «የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳልን» የሚል ቃል ገብቶበታል። እኔ የክርስቶስ ወንጌለ መንግሥት እንዲሰበክና እንዲስፋፋ ሕገ እግዚአብሔርና ቀኖና ቤተ ክርስቲያን እንደጠበቅ ጥረት የማደርግ እንጅ በማንም ላይ ማዕቀብ የመጣል ሥልጣን የለኝም - በአመፀኞች ላይ ማዕቀብ መጣል የሚችሉ የዚህ ዓለም መንግሥታት ናቸው።

ስለሆነም በእርስዎ በኩል ከሕገ ቤተ ክርስቲያን ውጪ በፈፀሙት ነገር ታግዶ የቆየው የክህነት ሥልጣንዎ በንስሐ ይመለስልዎ ዘንድ ከዚህ ደብዳቤ ጋር አያይዤ በላክሁልዎት በሌላ ደብዳቤ ላይ የተገለጸውን ቀኖናዊ ቅጣት ፈጽመው ሲጨርሱ የክህነቱ ሥልጣን እግድ የሚነሳ መሆኑን በአክብሮት እገልጽልዎታለሁ።

ከዚህ በተረፈ እግዱን አክብረውና ጠብቀው ለቆዩ ምእመናን ምስጋና ይገባቸዋል።

የቀኖና ቡራኬው ያልተፈጸመለት ቤተ ክርስቲያንም በሐዲስ መንፈስ በቅብዓ ሜሮን ታትሞ አገልግሎት እንዲሰጥ የሚደረግ መሆኑን ጨምሬ አሳስባለሁ።

 

ፍትህ መንፈሳዊ ፍትሃ ነገሥት

ባስ 94 «ወኢይሕንፁ ቤተ ክርስቲያን ዘእንበለ በትዕዛዘ ኤጲስ ቆጶስ» ባስልዮስ በ 94ኛው አንቀፅ «ያለ ኤጲስ ቆጶስ አንድም ያለ መጽሐፍ ትዕዛዝ ቤተ ክርስቲያን አይሥሩ»

«ወለ እመ ታሀበለ ፩ሂ ወገብረ ካልኣ እምዝንቱ ኢይቅረብ ቁርባነ ውስቴታ እስከ ለዓለም - ከኤጲስ ቆጶሱ ፈቃድ አንድም ከመጽሐፍ ትዕዛዝ ወጥቶ አንዱ ቢሠራ ለዘለዓለሙ አይቁረብባት፤ አንድም ኢይትቄረብ ይላል - ለዘለዓለሙ አይቆረብባት እንደ ገበያ እንደ በረት ፈት ሁና ትኑር » «ወለ እመ ተኅበለ ካህን ዘንተ ወቀርበ በውስቴታ ቁርባነ ይትመተር - ካህን ደፍሮ ቢሰዋ ቢቆርብባት ከሹመቱ ይሻር» ስለሚል በዚህ መሠረት ከክህነት የታገደው ካህን ወደ አገደው ሊቀ ጳጳስ ቀርቦ ቀኖናዊ ቅጣት ተቀብሎ ክህነቱ ሊመለስለት፣ ውግዘቱ ሊነሳለት ይችላል፤ ከዚህ ሌላ በፍትህ መንፈሳዊ አንቀጽ ራብዕ እንዲሁም በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 32 ከቁጥር 1 እስከ 10 የቅዱስ ፓትርያርክን ተግባር እና ኃላፊነት አስመልክቶ በተደነገገው መሠረት ፓትርያርኩ የሊቀ ጳጳሱን ውግዘት ያነሳል የሚል የለም። ሊቃነ ጳጳሳቱ ከሦስቱ ማዕረጋተ ክህነት ውስጥ ናቸውና - ጵጵስና፣ ቅስና፣ዲቁና። ፓትርያርክ ከዚህ ውስጥ ነው። ሊቀ ጳጳስ ፓትርያርክ ይባላል። ስለዚህ ከሊቃነ ጳጳሳቱ ጋር በክህነት አንድ ስለሆነ የሊቀ ጳጳስን ውግዘት እንደሚያነሳ አንዳችም አመላካች ቀኖና የለም።

የቋሚ ሲኖዶስ ተግባርና ኃላፊነትም በአንቀጽ 28 ከቁጥር 1 እስከ 12 በተደነገገው መሠረት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ያሳለፈውን ውሳኔ ማስፈጸም ነው እንጂ አንድ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ያወገዘውን ውግዘት የማንሳት ስልጣን እንደሌለው የታወቀ ነው። ይህም የቀኖና ጥሰት በመሆኑ ወደ አንቀጽ 32 እንዳያመራን ጥንቃቄ ያስፈልገናል። ስለዚህ እንዲህ ያሉትን ውሳኔዎች ለመቀበል ከባድ ስለሆነ ሁሉንም ነገር ለምልዓተ ጉባኤው መተው መፍትሄ ነው እላለሁ።

 

እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክ

 

ግልባጭ፦

-       ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት
-      
ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት
-      
ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት
አዲስ አበባ

-       ለሰሜን ምሥራቅ ደቡብ ምሥራቅና መካከለኛው አሜሪካ
ኒው ዮርክ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት፣ ኒውዮርክ

IMAGE0004.JPG
letter_01_1.jpg
letter_01_2.jpg
leter_01_3.jpg