ቋሚ ሲኖዶስ ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ የያዙትን ሥልጣነ ክህነት የማንሳት ሥልጣን እንደሌለው አምኖ የቦስተኑ ሊቀ ጉባኤ ኤርምያስ ወልደ ኢየሱስን ጉዳይ ወደ ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ መራው

-       በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የተያዘባቸውን ሥልጣነ ክህነት በቋሚ ሲኖዶስ በኩል ለማስመለስ የሄዱትን የቦስተኑ ሊቀ ጉባኤ ኤርምያስ ወልደ ኢየሱስን ጉዳይ መርምሮ መወሰን ሥልጣኑ እንዳልሆነ የተረዳው ቋሚ ሲኖዶስ ጉዳዩን ወደ ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ መራው።

-       ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ ከሳምንታት በፊት ለሚኒያፖሊሱ መሪጌታ ጌታሁን «ሥልጣነ ክህነትህን መልሼልሃለሁ» ያለው ቋሚ ሲኖዶስ ይህን የማድረግ ሥልጣን እንደሌለው አስገንዝበው የመሪጌታ ጌታሁን መኮንን ውግዘት አሁንም እንደጸና ነው ማለታቸው አይዘነጋም። ያን ጊዜም ያስገነዘቡት ይህንን ነበር ዛሬም የተወሰነው ይህ ነው - ቋሚ ሲኖዶስ አንድ ሊቀ ጳጳስ የያዘውን ሥልጣነ ክህነት የማንሳት ሥልጣን ሕገ ሲኖዶስ አልሰጠውም- ከዚህ በፊትም ተደርጎም አያውቅም! በዛሬም ውሳኔም የጸናው ይህ ሕግ ነው

ቤተ ክርስቲያን ባላት የአቅም ውሱንነት የተነሳ ልክ እንደ አገር ቤቱ ሥርዓት አስይዛ ልታስተዳድረው የከበዳት የባሕር ማዶው አገልግሎቷ በተለይ በሰሜን አሜሪካ አያሌ ፈተናዎችን እያመጣባት ይገኛል። ካህኑን እንደ አንድ ደመወዝ ተቀባይ ሠራተኛ እንጂ እንደ ካህን የማያከብር ምእመን የመብዛቱን ያኽል፣ ለሊቀ ጳጳስ ትዕዛዝ ምንም ደንታ የሌላቸውና የሊቀ ጳጳስን ቃል የማይሰሙ፣ ሀገረ ስብከትን የማያውቁ፣ ሀገረ ስብከትም የማያውቃቸው ካህናትም ቤተ ክርስቲያንን እንደ ግል ንብረት በየማዕዘኑ እየከፈቱና እየዘጉ መኖርን አሜሪካ የሰጠቻቸው መብት አድርገው የሚቆጥሩ በየግዛቱ አሉ። ይህንንም ፈተና በየአስተዳደር ዘመናቸው ከቅዱስ ሲኖዶስ ተመድበው የሚመጡ ሊቃነ ጳጳሳት ምዕመናኑም ሆነ ካህናቱ በሰሟቸው መጠን ልክ ለመፍታት የተቻላቸውን ሲያደርጉ ቆይተዋል።

«ከሰው ጋር ምን አጋጨዎት አይተው እንዳላዩ ማለፉ ይሻላል፣ አገሩ አሜሪካ ነው!» የሚል መካሪ ሲመጣ «ይሁን፣ እሺ» ብለው ማለፍን የመረጡ ያሉትን ያኽል የሀገረ ስብከታችን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ በተሰጣቸው መንፈሳዊ ኃላፊነት እና ሥልጣን ከሥርዓት ያፈነገጡትን በርካቶችን መክረው እና አስተምረው መልሰዋል፣ የአብያተ ክርስቲያናቱንም ቁጥር ከ8 ወደ 34 አሳድገዋል፣ በእንቢተኛነት አሻፈረኝ ያሉትንም ሕገ ቤተ ክርስርቲያን በሚፈቅደው መሠረት ሥልጣነ ክህነታቸውን እስከመያዝ ድረስ በመሄድ ሀገረ ስብከታቸውን እና ቤተ ክርስቲያንን አስከብረዋል።

ከእነዚህም ካህናት መካከል የቦስተኑ ሊቀ ጉባኤ ኤርምያስ ወልደ ኢየሱስ አንዱ ነበሩ። አስቀድመው ያገለግሉበት ከነበረው ቤተ ክርስቲያን ካህናት እና ምእመናን ጋር በተነሳ የግል አለመግባባት ምክንያት የራሴ ቤተ ክርስቲያን እመሠርታለሁ ብለው ሲያቅዱ በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የአዲስ ቤተ ክርስቲያን መመሥረትን አስፈላጊነት ሳይታመንበትና ሳይፈቀድ ለራስ ጥቅም በራስ ፈቃድ ብቻ ይህን ማድረግ አግባብ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ የተነገራቸውን ትዕዛዝ ችላ በማለት ከሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም ዘንድ አምጥቸዋለሁ ባሉት ታቦት አዲስ ቤተ ክርስቲያን በማን አለብኝነት መመሥረታቸውን ተከትሎ በሀገረ ስብከታችን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ ሥልጣነ ክህነታቸው ተይዞባቸዋል።

ሊቀ ጉባኤ ኤርምያስ ከዚህ በፊት ይህንን ውግዘት ለማስነሳት ወደ ቅዱስ ሲኖዶስ ሄደው የነበረ ቢሆንም ቅዱስ ሲኖዶስ ሥልጣነ ክህነታቸው የተያዘው አግባብነት ባለው ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መሆኑን ጠቅሶ «ሥልጣነ ክህነትዎን ከያዙት ከሀገረ ስብከትዎ ሊቀ ጳጳስ ጋር ይጨርሱ» በማለት ቢያሰናብታቸውም ያንን ማስፈጸሙን ችላ ብለው እንዲሁ ሲኖሩ ቆይተዋል። አንዱ በቀደደው ቀዳዳ ሌላው ይገባልና የሚኒያፖሊሱ መሪጌታ ጌታሁን መኮንን ሕገ ቤተ ክርስቲያንን በመጣሱ ምክንያት ተወግዞ ለሦስት ዓመት ምንም ሥልጣነ ክህነት ሳይኖረው ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን ሲፈጽም ኖሮ ወደ ቋሚ ሲኖዶስ በመሄድ በአንዲት ማመልከቻ ክህነቴን አስመልሼ፣ ታቦት ተሰጥቶኝ፣ አዲስ ቤተ ክርስቲያን ለመመሥረትም ፈቃድ አግኝቼ፣ ይህንንም ቤተ ክርስቲያን ይባርኩ ዘንድ አቡነ ዳንኤል ከኢትዮጵያ ወደ ሚኒያፖሊስ ተልከውልኝ መጣሁ የሚለውን ወሬ አዕምሮ እንደሌለው ሰው ምንም ሳያገናዝቡ እንደ ገደል ማሚቶ በዓለሙ ለመንገር እንቅልፍ አጥተው በሚጽፉ የኢንተርኔት ክፉ መናፍስት ሲያሰራጭ ሊቀ ጉባኤም ስለሰሙ እርሳቸውም በዚያው ቀዳዳ ለመግባት የቻሉትን ሁሉ ጥረት አድርገው ነበር።

የሦስት ወር የሥራ ዘመኑን ሊያገባድድ ሁለት ሳምንት ሲቀረው ጉዳዩ ቀርቦለት በአንድ ቀን ውስጥ ለመሪጌታ ጌታሁን «ውግዘትህን አንስቸልሃለሁ» ያለው ተሰናባቹ ቋሚ ሲኖዶስ የሥራ ዘመኑን አገባድዶ በአዲስ በመተካቱ የሊቀ ጉባኤን ጉዳይ ያየው ለሚቀጥሉት ሦስት ወራት የሚያገለግለው ተረኛው ቋሚ ሲኖዶስ ነበር።

ወደፊት በጊዜው በዝርዝር በምንተነትነውና ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ ለቅዱስ ፓትርያርኩ እና ለቋሚ ሲኖዶስ አባላት በግልም በጋራም በሰጡት መንፈሳዊ ቁርጠኛነትን የሚጠይቅ የቀኖና ቤተ ክርስቲያን አተረጓጎም ትንታኔ ይህንን ጉዳይ የማየት ምንም ዓይነት ሥልጣን እንደሌለው የተረዳው ቋሚ ሲኖዶስ ጉዳዩ እንደ ሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ክህነቱን ወደያዘው የክፍሉ ሊቀ ጳጳስ እንዲመራ ከመወሰን ውጪ ምንም አማራጭ ስላልነበረው «የተያዘብኝን ሥልጣነ ክህነት ቋሚ ሲኖዶስ ያንሳልኝ» ብለው ሊቀ ጉባኤ ኤርምያስ ወልደ ኢየሱስ ያቀረቡትን ጥያቄ ወደ ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ መርቶታል።

*** ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ ይህንን አስመልክቶ ያስተላለፉትን ውሳኔ ሰሞኑን በስፋት እናሳውቃለን ***

ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ ከሳምንታት በፊት ለሚኒያፖሊሱ መሪጌታ ጌታሁን «ሥልጣነ ክህነትህን መልሼልሃለሁ» ያለው ቋሚ ሲኖዶስ ይህን የማድረግ ሥልጣን እንደሌለው አስገንዝበው የመሪጌታ ጌታሁን መኮንን ውግዘት አሁንም እንደጸና ነው ማለታቸው አይዘነጋም። ያን ጊዜም ያሉት ይህንን ነበር ዛሬም የተወሰነው ይህ ነው - ቋሚ ሲኖዶስ አንድ ሊቀ ጳጳስ የያዘውን ሥልጣነ ክህነት የማንሳት ሥልጣን ሕገ ሲኖዶስ አልሰጠውም- ከዚህ በፊትም ተደርጎም አያውቅም!