ቋሚ ሲኖዶስ «አንስቻለሁ» ያለው የሚኒያፖሊሱ መሪጌታ ጌታሁን መኮንን ውግዘት እንደፀና ነው ፣ የአቡነ ዳንኤል ተደጋጋሚ ጣልቃ ገብነት እና ትምህርትም የሚያስወግዝ ነው /ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ/

0000.PNG

 

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰሜን ምሥራቅ ደቡብ ምሥራቅና መካከለኛው አሜሪካ ኒውዮርክ ሀገረ ስብከት ሥር የምትገኙ መምህራነ ወንጌል፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ካህናት ወዲያቆናት፣ ምእመናን ወምእመናት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት፤ ተአምኁ በበይናቲክሙ በአምኃ ተፋቅሮ ወተሰነአው ኩልክሙ እለ በክርስቶስ ሀሎክሙ ጸጋ ምስለ ኩልክሙ

መልእክተ ጴጥሮስ ቀዳሚት ምዕራፍ 5ቱ ወኁልቁ 104 ወትርጓሜሁ ከመዝ እርስ በርሳችሁ ሰላም ሰላም ተባባሉ እጅ ተነሣሡ ሁላችሁ በክርስቶስ ያላችሁ ጸጋ ይብዛላችሁ። ወብዙኅ ብየ ዘእጽሕፍ ለክሙ ወኢፈቀድኩ በክርታስ ወበማየ ሕመት እጽሐፍ ለክሙ መል. ዮሐ. ዳግሚት ምዕ 1 ቁጥር 12 - የምጽፍላችሁ ብዙ ነገር ነበረኝ ነገር ግን ስለ ክብራችሁ በወረቀትና በጥቁር ቀለም ልጽፍላችሁ አልወደድሁም። ብዙኃን መስሕታን መጽኡ ኅቤክሙ ወዝ ውእቱ መስሐቲ ሐሳዊ ያነ መሲሕ - ማለትም ክርስቶስ አምላክ አይደለም ብለው የሚያስተባብሉ ወደ እናንተ መጥተዋል። መልእክተ ዮሐንስ ዳግሚትን መላልሶ ማንበብ ስለ ሐሳዌ መሲሕ መነሳት መረዳት እንችላለን። በዚህ አንጻር ብፁዕ አቡነ ዳንኤል ባለፉት ዓመታት ወደ ሚኒሶታ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ገብተው ወልድ ወደ ሰማይ ሲያርግ ደከመ ተቸገረ ወደ አባቱ ለመነ የሚል አርዮሳዊ ትምህርት በማስተላለፋቸው ብዙዎች የተዋሕዶ ምእመናንን ያሳዘነ እና ያስለቀሰ ነበር።

ይኸውም በምስል በድምጽ በቪዲዮ ተዘጋጅቶ ለዓለም በመሠራጨቱ የቦታው አስተዳዳሪ ነኝ ብለው የተቀመጡት ሊቀ ትጉሐን ጌታሁን መኮንንም ይህ አርዮሳዊ የወልድ ፍጡር ትምህርት ሲሠጥ ዝም ብለው በማዳመጣቸውና ከዚያ በፊትም በተለያየ ሐይማኖታዊ ቀኖናዊ ስህተት በመፈፀማቸው ሁለቱንም አውግዘናቸው ቆይተን ነበር «ወእግዚአብሔር ይስዕሮሙ ለክልኤሆሙ» 1ኛ ቆሮ. 613 እንዲል። ይባስ ብሎም በዚህ ሰሞን ደግሞ ይህ ውግዘት አስተዳደራዊ ነው እንጂ ሐይማኖታዊ አይደለም ተብሎ በቋሚ ሲኖዶስ «አንስተናል» የሚል ደብዳቤ ተጽፎአል።

ይሁን እንጂ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 28 ከቁጥር 1 -12 በተዘረዘረው መሠረት አንድ ሊቀ ጳጳስ ያሳለፈውን ውግዘት ቋሚ ሲኖዶስ ማንሳት እንደሚችል የሚያመላክት ሥልጣን የለውም፤ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች ከማስፈጸም በስተቀር። ስለዚህ ውግዘቱ አቡነ ዳንኤልን ጨምሮ የጸና ስለሆነ በሚኒያፖሊስ ከተማ አዲስ ተከፈተ እየተባለ በሚነገረው ቤተ ክርስቲያን ማንኛውም የተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች እንዳይሳተፉ! ይህን ማድረግ ከክህደቱ ጋር መተባበር ነውና - እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ፦ «ለመስተካህድ ብእሲ እም ከመ ምዕረ ወካዕበ ገሠፅኮ ወአበየ ህድጎ ወአምሮ ከመ አላዊ ውዕቱ ዘከማሁ ያስህት ወያጌጊ ወይረክብ ኩነኔ» ቲቶ 3 1-12

ትርጉም፦

አንድን ከሐዲ ሰው አንድ ጊዜ ሁለት ጊዜ ከገሠፅከው በኋላ ምዕመናንን በክህደት ኑፋቄ እንዳይስብ የዘለዓለም ፍርድ የሚጠብቀው አላዊ ነውና ከእርሱ ተለይ፣ ነገር ግን ክህደቱን እና ኑፋቄውን ለምእመናን አስታውቅበት። ስለዚህ ሁላችሁም ይህንን አውቃችሁ ከቦታው ከመሄድና መስቀልም ከመሳለም ጥንቃቄ እንድታደርጉ እናስታውቃለን።

ማሳሰቢያ፦

ከዚህ በፊት ቅዱስ ሲኖዶስ በላከው ደብዳቤ እንዳስታወቀው ሁሉ የአቡነ ዳንኤል ጣልቃ ገብነት ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ከቁጥር 156-161 ያለውን የሚተላፍና የሚሽር በመሆኑ የሚያስወግዛቸው መሆኑን እና በሊቀ ትጉሐን ጌታሁን መኮንን ያለውም ውግዘት ንስሐ ገብተው እስኪመለሱ ድረስ እንደፀና መሆኑን እንዲታወቅ። 

            
                                                  እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክ

ግልባጭ፦

- ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት
- ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት
- ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት
  አዲስ አበባ

 

coverImage.jpg
allPages0002.jpg