ራዕይና ተልዕኮ

 የእግዚአብሔር ቃል ሰው ያለ ራዕይ መኖር የማይችል መሆኑን ሲያረጋግጥ «ራዕይ ባይኖር ሕዝብ መረን ይሆናል» (ምሳ.፳፱፣ ፲፰) ይላል። የሰው ልጅ ዓለምን በኃላፊነት ሊመራ ከእግዚአብሔር በአደራ የተቀበለ ባለ ራዕይ ነው። ከሰማይ እስከ ምድር፤ ከረቂቅ እስከ ግዙፍ፤ በሚታይና በማይታየው ፍጥረት ሁሉ የመጠቀም መብት የተሰጠው በእግዚአብሔር አምሳል ለተፈጠረው የሰው ልጅ ብቻ ነው። ከሥነ ፍጥረታት ሁሉ ሰውን የሚያልቀውና ልዩ፤ ክቡር ፍጥረት የሚያደርገው «ባለ አእምሮ» መሆኑ ነው። «እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ በተሰጠኝ ጸጋ እናገራለሁ»(ሮሜ ፲፪፣፫) እንዲል። በዘመናችን የሚታየው የሳይንስና የሥነ ቴክኖሎጂ ፍሰትም የዚሁ የሰው ልጅ አእምሮ ግኝት ነው። የትኛውም የሥነ ጥበብ ቴክኖሎጂ የበጎም የክፉም መገልገያ መሣሪያ ሊሆን ይችላል። ወሳኝነቱ አእምሮ ስለሆነ የተጠያቂነት ኃላፊነቱ የሰው ልጅ ነው። ዓለምን አንድ መንደር ያደረገው መገናኛ ብዙኃን ሁሉ የሰው ልጅ እይታና ሀሳብ ማስተላለፊያ ሲሆን ጉዳቱና ጥቅሙ የሚለካው በአእምሮ ሚዛን ነው። አእምሮ በእውቀት፤ በእምነትና በማስተዋል የተዘጋጀ ከሆነ ራዕዩና ተልዕኮው በትክክል ግቡን ሊመታ ይችላል። ከዚህም የተነሳ ቴክኖሎጂ የእግዚአብሔር የጸጋ ፍሰትና የሰው ልጅ የእምሮ ምጥቀት መሆኑን እንረዳለን። በምድር ላይ ልትተገብረው መለኮታዊ ራዕይና ተልዕኮ ለተሰጣት ቤተ ክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን ከአለፈው የዘመነ አበው አገልግሎት በላይ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን መረዳት ይቻላል። ዛሬ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች በአንድ ማዕድ ወንጌልን ይማራሉ። በዓለም ዙሪያ ያለች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልዕኮዋና የዕለት እንቅስቃሴዋ በአንድ ጊዜ በሁሉም ሥፍራ ይነበባል። ይኽም በብዙ መቶ ማይል ተራርቀው ላሉት ነፍሳት ብርታትና እድገት መሆኑ የሚታመን ነው። በመሆኑም ይኽ ድኅረ ገጽ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ራዕይንና ተልዕኮን የሚያንፀባርቅ፤ የሀገረ ስብከታችንን ወቅታዊ እንቅስቃሴ የሚያበሥር ሆኖ መንፈሳዊ ግልጋሎቶችን ለመስጠት የቆመ ነው።

 ዓላማ

 የዚህ ድረ ገጽ ተቀዳሚ ዓላማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ራዕይንና ተልዕኮን መፈጸምና ማስፈጸም ሲሆን የሚከተሉት ተግባራት ይገኙበታል።

1. የቅዱስ ሲኖዶስን መመሪያና ጥሪ በወቅቱ ለማስተላለፍ

2. ሀገረ ስብከቱ በሥሩ ላሉት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የሚያስተላልፋቸው መመሪያዎች በፍጥነት ተደራሽ እንዲሆኑና ለሕዝብ ጆሮም መድረስ እንዲችሉ ማድረግ

3. የቤተ ክርስቲያንዋን ሕግና ቀኖና ለመጠበቅና ለማስጠበቅ ይቻል ዘንድ ትምህርቶችንና መልእክቶችን እያዘጋጀ ለማስተማር

4. የሀገረ ስብከቱንና የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትን መዋቅራዊ አሠራርን በመከተል የጋራ ተልዕኮ የሆነውን የስብከተ ወንጌል ሥርጭትን ለማቀላጠፍ

5. በሀገረ ስብከታችን ያለውን መንፈሳዊ እንቅስቃሴን አስመልክቶ ለምዕመናን ብርታት የሆኑ ልምዶችንና ተግዳሮቶችን ለማካፈል ድረ ገጹ ከላይ ከተዘረዘሩት ተግባራት ሌላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሀብት የሆኑ ያሬዳዊ ድርሰቶችን ያስተላልፋል። የገዳማትና የመካነ ቅዱሳን ታሪክና ሥነ ቅርስን ያስቃኛል። በመሆኑም ትውልዱ ቅድስት ሀገሩንና እናት ቤተ ክርስቲያኑን እንዲያውቅ ታላቅ ዕድልን በመስጠት የቤተ ክርስቲያንዋ የበላይ ወሳኝ አካል የሆነውን የቅዱስ ሲኖዶስን ድምጽ ያሰማል።

 ወስብሐት ለእግዚአብሔር!