በምድረ ኢትዮጵያ የኖሩና ለኢትዮጵያ መጠሪያ የሆኑ ፤ የካም ልጆችና የልጅ ልጆች

ከክርስቶስ ልደት በፊት በ3600 (ሦስት ሺህ ስድስት መቶ) ዓ.ዓ በየመን ይኖሩ ከነበሩ ከነገደ ሴም የተከፈሉ ራሳቸውን ነገደ ዮቅጣን በማለት በባብኤል መንደር (የመከራ በር) በኩል ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል፡፡ ዮቅጣን አማርኛ መጠሪያቸው ሲሆን በግዕዝ ዮቃጤን በአውሮፓውያን የካታን ይባላሉ፡፡ ዮቅጣን አስራሶስት ልጆች የነበሩት ሲሆን መኖሪያቸው የነበረውም በእስያ ምድር ከሜሻ እስከ ፋርስ እስከ ምሥራቅ ተራራ ነበር (ዘፍ 10፡-በሙሉ) ከነዚህም ከአሥራ ሦስቱ ልጆች አምስቱ ሳባ፣ ይባል ፣አፈር ፣አሲማኤል፣ ኤውላጥ፣ ቦታ ስለጠበባቸው ከወንድሞቻቸው ተለይተው የእስያ ደቡብ ወደሚሆን ወደ የመን መጡ፡፡

የየመንም ብልሃትና ጥበብ ተምረው በመልካም ኑሮ ሲኖሩ የህንድ ነገሥታት ጦር እየሰደዱ የመንን እየወጉ ስላወካቸው ሶስቱ ሳባ ይባልና አፈር ሁለቱን ወንድሞቻቸው ጥለው የነገደ ካም ወገን ጰኦሪ 1ኛ በነገሠበት ዘመን ወደ ኢትዮጵያ ገቡ፡፡ ከጥቂት ዘመናት በሁዋላ እነዚህ ሶስቱ ነገደ ዮቅጣን እርስ በእርሳቸው ካለመስማማታቸው የተነሣ ተለያይተው ለየብቻቸው ሀገር ያዙ የያዙዋቸው የሀገሪቱ ክፍሎችም ሳባ ትግሬን ይባል አዳልን ኦፈር ውጋዴንን ይዘው ቀርተዋል፡፡

ከነገደ ካም ወገን በኢትዮጵያ ነግሦ የነበረው ጶኦሪ 1ኛ እነዚህ ሦስቱን ነገደ ዮቅጣንን አምስት ዓመት አስገብራቸዋል በሁዋላ ግን ራማ የሚባል የሕንድ ንጉሥ ወደ ኦትዮጵያ መጥቶ ጶኦሪን ወግቶ መንግሥቱን በወሰደበት ጊዜ እነዚህ ሶስት ነገዶች ዮቅጣን ከውጋዴን ከአዳልና ከትግሬ ተላልከውና ተስማምተው በትግሬ ላይ ከነበረው ከሳባ ዘር አከሁናስን ሳባ 2ኛ ብለው አንግሰው ከህንዱ ንጉሥ ከራማ ጋር ተዋግተው ድል አድርገው ገደሉት እነርሱም አገሪቱን ኢትዮጵያን ከመግዛት ህዝቡን ከባርነት ነፃ ስላወጡ አግዓዝያን ተባሉ በግእዝ አግዓዚ ነፃ አወጣ ማለት ነው፡፡ አግዓዚያን ማለት ግን ነፃ የሚያወጡ ማለት ነው፡፡

እነዚህ ነገደ ዮቅጣን ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በንግሥና ተራ ከተቀመጡ በሁዋላ በዚህች አገር ከሚኖሩ ከኩሽ ዘሮች ጋር እየተጋቡና እየበረከቱ ሄደዋል፡፡ በዚህን  ጊዜ ይችን ሀገር ምድረ እግዚት ነፃ የሆነች ሀገር ሲሉ ሕዝቦቹን ምድረ አግአዚያን የነፃነት ባለቤቶች ነፃነት ያለቸው ሰዎች መኖሪያ ብለው ጠርተዋቸዋል፡፡ ይህን አስመልክቶ በድርሳነ ዑራኤል ላይ እንደተገለፀው ኢትዮጵያ ነፃ የሆነች ሀገር ናት በእናቱ እግር መመላለስ ተባርካለች ይላል፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት ነገደ ዮቅጣን መንገሥ ከጀመሩበት ከ1985-982ዓ.ዓ ለ1003 ዓመታት ያህል የነገሡት የዮቅጣን ነገዶች ሃምሣ ሁለት ናቸው፡፡(የብላቴን ጌታ ኅሩይ መፅሐፍ ‹‹ዋዜማን ይመልከቱ)

በታሪክ እንደተገለፀው በብሉያ ኪዳን ከነበሩት የመጀመሪያዎቹ ነገሥታት ሃያ ሰባተኛው ንጉሥ የነበረው ኩሽ በሁለተኛ ስሙ ‹‹ኢትዮጲስ›› ተብሎ ይጠራ ነበር፡፡ ስለዚህ ከእርሱ ስም በመነሣት ሃገሪቱ ዛሬ የምትጠራበት ስም ኢትዮጵያ የሚለውን ይዛ ቀርታለች፡፡ ሌሎች ወገኖች እንደሚሉት ደግሞ ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ከግሪኮች የተወረሠ ነው ይላሉ፡፡ ይኸውም ኤቶስና ኦድሲስ ከሚለው ግሥ የወጣ ሲሆን ‹‹ኤቶስ›› ማለት ዋዕይ በረሃማ ሙቀታማ ማለት ነው፡፡ ‹‹ኦጲሲስ›› ማለት ደግሞ ገፅ አርአያው በጠየመ (የወየበ) ህዝብ ማለት ነው፡፡ ሁለቱ ቃላት ሲጣመሩ ‹‹ኤቴአፒያ›› ወይም ‹‹ኤቴኦጲስ›› የሚል ቃል ይወጣዋል‹‹ኤቴኦፒያ›› ቢል የሀገራቱን ቆላነት ያመለክታል ቆላ በረሃ ዋዕይ የትኩሳት ሀገር ማለት ነው ኢቴኦፒያ ቢል የሕዝቡን ምንነት ያመለክታል በዋዕይ ፀሐይ ፊቱ የጠቆረ የበረሃ የቆላ ሻንቅላ ማለት ነው ይህንንም ስያሜ በሰጣት የተሳሳተ አመለካከት ይዘው ነው፡፡

በአዲሱ የኢብራይስጥ መፅሐፍ ቅዱስ ላይ ኢትዮጲ የሚለውን በርሃ ብለው ሰይመውታል ይኽውም እንደ ቃዲስ በርኔንና ሲና በርሃ ቆጥረዋት ነው፡፡ የምዕራባውያን የታሪክ አባት ተብሎ የሚጠራው ሔሮድቱስ ስለኢትዮጵያ ባነሳበት መፅሐፍ ኢትዮጵያውያን በውበት በቁመትና በሐይል ከሰዎች ሁሉ የሚበልጡ ናቸው ብሉአል፡፡

በሆሜር መፅሐፍ ቀዩን ወይን ኢትዮጵያ ስለሚለው ኢትዮጵያዊ ማለት ቀይ የቀይ ዳማ ቀለም ያለው ሕዝብ ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያዊያን አባት ኩሽ በሞተ በ2450 ዓመት በ(284 ዓ.ም) በታላቅነቱና በገናናነቱ በዓለም ገኖ የሚታወቀው በጥሊሞስ በነገሠበት ዘመን የብሉይ ኪዳን  መፅሐፍትና በዕብራይስጥ ወደ ፅርዕ የለወጡ ሰባው ሊቃውንት ሙሴ ኩሽ እያለ የተፃፈውን ኢትዮጵያ ብለው ፅፈዋል (ለውጠዋል)፡፡ ሊቀ ጠበብት አያሌው ታምሩ  በ1953 ዓ.ም ባሳተሙት ‹‹የኢትዮጵያ እምነት በሦስቱ ህግጋት›› በተሰኘው መፅሐፋቸው (ከገፅ 54-58) ስለ ኢትዮጵያ መጠሪያ ሲገልፅ ሌሎች የኢትዮጵያ ስያሜዎች ከመታሰቢያ ውስጥ ሆኖ ኢትዮጵያ የሚለው በቤቴል አንፃር ይጠራል ቤቴል ማለትም የእግዚአብሔር ቤት ማለት እንደሆነ ሁሉ ኢትዮጵያ ማለትም ሀገረ እግዚአብሔር ማለት ነው፡፡ ስምነቱን ስንማረውም ትርጓሜው እንደሚከተለው ነው፡፡

     ኢ - ማለት እግዚአብሔር (አሌፍ አልፋ)
     ት - ማለት ታው ትጉህ አብ
     ዮ - ማለት ዮድ የማን እግዚአብሔር ወልድ
     ጵ - ማለት ጰራቅሊጦስ መንፈስ ቅዱስ
     ያ - ማለት የአንድ አምላክ የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ሀገር ማለት ነው በማለት አስቀምጠዋል፡፡