ጸሎት ከመጽሐፍ ቅዱስ

ጸሎት ከመጽሐፍ ቅዱስ

አባታችን ሆይ

 አባታችን ሆይ፤ በሰማያት የምትኖር፤ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁም በምድር ትሁን። የዕለት እንጀራችንን ስጠን ለዛሬ፤ በደላችንንም ይቅር በለን፤ እኛም የበደሉንን ይቅር እንደምንል፤ አቤቱ ወደ ፈተናም አታግባን፤ ከክፉ ሁሉ አድነን እንጂ፤ መንግሥት የአንተ ናትና  ኃይል ክብር ምስጋና ለዘለዓለሙ አሜን!

 የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎት - የሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ ፩፤፵፯-፶፭

ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፥ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤ የባሪያይቱን ውርደት ተመልክቶአልና። እነሆም፥ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፤ ብርቱ የሆነ እርሱ በእኔ ታላቅ ሥራ አድርጎአልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው። ምሕረቱም ለሚፈሩት እስከ ትውልድና ትውልድ ይኖራል። በክንዱ ኃይል አድርጎአል፤ ትዕቢተኞችን በልባቸው አሳብ በትኖአል፤ ገዥዎችን ከዙፋናቸው አዋርዶአል፤ ትሑታንንም ከፍ አድርጎአል፤ የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቦአል፤ ባለ ጠጎችንም ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል። ለአባቶቻችን እንደ ተናገረ፥ ለአብርሃምና ለዘሩ ለዘላለም ምሕረቱ ትዝ እያለው እስራኤልን ብላቴናውን ረድቶአል።

የነቢዩ ዳንኤል ጸሎት - ትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ ፱፤ ፬-፲፱

ጌታ ሆይ፥ ከሚወድዱህና ትእዛዝህን ከሚፈጽሙ ጋር ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ ታላቅና የምታስፈራ አምላክ ሆይ፥ ኃጢአትን ሠርተናል፥ በድለንማል፥ ክፋትንም አድርገናል፥ ዐምፀንማል፥ ከትእዛዝህና ከፍርድህም ፈቀቅ ብለናል፤ በስምህም ለነገሥታቶቻችንና ለአለቆቻችን ለአባቶቻችንም ለአገሩም ሕዝብ ሁሉ የተናገሩትን ባሪያዎችህን ነቢያትን አልሰማንም። ጌታ ሆይ፥ ጽድቅ ለአንተ ነው፤ እንደ ዛሬም ለእኛ ለይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም ለሚቀመጡ ለእስራኤልም ሁሉ በቅርብና በሩቅም ላሉት አንተን በበደሉበት በበደላቸው ምክንያት በበተንህበት አገር ሁሉ የፊት እፍረት ነው። ጌታ ሆይ፥ በአንተ ላይ ኃጢአት ስለ ሠራን ለእኛና ለነገሥታቶቻችን ለአለቆቻችንና ለአባቶቻችንም የፊት እፍረት ነው። በእርሱ ላይ ምንም እንኳ ያመፅን ብንሆን፥ በባሪያዎቹም በነቢያት እጅ በፊታችን ባኖረው በሕጉ እንሄድ ዘንድ የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ቃል ምንም እንኳ ባንሰማ፥ ለጌታ ለአምላካችን ምሕረትና ይቅርታ ነው። እስራኤልም ሁሉ ሕግህን ተላልፈዋል፥ ቃልህንም እንዳይሰሙ ፈቀቅ ብለዋል፤ በእርሱ ላይ ኃጢአት ሠርተናልና በእግዚአብሔር ባሪያ በሙሴ ሕግ የተጻፈው መሐላና እርግማን ፈሰሰብን። እጅግ ክፉ ነገርንም በእኛ ላይ በማምጣቱ በላያችንና በእኛ ዘንድ በተሾሙት ፈራጆቻችን ላይ የተናገረውን ቃል አጸና፤ በኢየሩሳሌምም ላይ እንደ ተደረገው ያለ ነገር ከቶ ከሰማይ ሁሉ በታች አልተደረገም። በሙሴም ሕግ እንደ ተጻፈ ይህ ክፉ ነገር ሁሉ መጣብን፤ ከኃጢአታችንም እንመለስ እውነትህንም እናስብ ዘንድ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ፊት አልለመንንም። ስለዚህም እግዚአብሔር ክፉ ነገሩን ጠብቆ በእኛ ላይ አመጣ፤ አምላካችን እግዚአብሔር በሚሠራው ሥራ ሁሉ ጻድቅ ነውና፥ እኛም ቃሉን አልሰማንምና። አሁንም ሕዝብህን ከግብጽ ምድር በበረታች እጅ ያወጣህ፥ እንደ ዛሬም ቀን ዝና ለአንተ ያገኘህ ጌታ አምላካችን ሆይ፥ ኃጢአትን ሠርተናል፥ ክፋትንም አድርገናል። ጌታ ሆይ፥ ስለ ኃጢአታችንና ስለ አባቶቻችን በደል ኢየሩሳሌምና ሕዝብህ በዙሪያችን ላሉት ሁሉ መሰደቢያ ሆነዋልና እንደ ጽድቅህ ሁሉ ቍጣህና መዓትህ ከከተማህ ከኢየሩሳሌም ከቅዱስ ተራራህ እንዲመለስ እለምንሃለሁ። አሁንም፥ አምላካችን ሆይ፥ የባሪያህን ጸሎትና ልመናውን ስማ፤ ጌታ ሆይ፥ በፈረሰው በመቅደስህ ላይ ስለ አንተ ስትል ፊትህን አብራ። አምላኬ ሆይ፥ በፊትህ የምንለምን ስለ ብዙ ምሕረትህ ነው እንጂ ስለ ጽድቃችን አይደለምና ጆሮህን አዘንብለህ ስማ፤ ዓይንህን ገልጠህ ጥፋታችንና ስምህ የተጠራባትን ከተማ ተመልከት።  አቤቱ፥ ስማ፤ አቤቱ፥ ይቅር በል፤ አቤቱ፥ አድምጥና አድርግ፤ አምላኬ ሆይ፥ ስምህ በከተማህና በሕዝብህ ላይ ተጠርቶአልና ስለ ራስህ አትዘግይ።

  የነቢየ እግዚአብሔር የቅዱስ ዳዊት ጸሎት - መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፲፮ (፲፯)፤፩-፲፭

አቤቱ፥ ጽድቄን ስማ ጩኸቴንም አድምጥ፤ በተንኰለኛም ከንፈር ያልሆነውን ጸሎቴን አድምጥ። ፍርዴ ከፊትህ ይውጣ፥ ዓይኖችህም በቅንነት ይዩ። ልቤን ፈተንኸው በሌሊትም ጐበኘኸኝ፤ ፈተንኸኝ፥ ምንም አላገኘህብኝም። የሰውን ሥራ አፌ እንዳይናገር ፈቃዴ ነው፤ ስለ ከንፈሮችህ ቃል ጭንቅ የሆኑ መንገዶችን ጠበቅሁ።  እግሮቼ እንዳይናወጡ አረማመዴን በመንገድህ አጽና። አቤቱ፥ ሰምተኸኛልና ወደ አንተ ጠራሁ፤ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፥ ቃሌንም ስማ። የሚያምኑህን ከሚቃወሙ በቀኝህ የምታድናቸው፥ ቸርነትህን ድንቅ አድርገህ ግለጠው።  እንደ ዓይን ብሌን ጠብቀኝ፥ በክንፎችህ ጥላ ሰውረኝ፥ ከሚያስጨንቁኝ ከኃጢአተኞች፥ ነፍሴንም ከሚከብቡአት ከጠላቶቼ። አንጀታቸውን በስብ ቋጠሩ፥ በአፋቸውም ትንቢትን ተናገሩ። አሁንም እርምጃችንን ከበቡ፤ ዓይናቸውን ወደ ምድር ዝቅ ዝቅ አደረጉ።  

እርሱ ንጥቂያን እንደሚናፍቅ አንበሳ ተሸጕጦም እንደሚኖር እንደ አንበሳ ደቦል ነው። አቤቱ፥ ተነሥ፤ ቀድመህ ወደ ታች ጣለው፤ ነፍሴን ከኃጢአተኛ በሰይፍህ አድናት። አቤቱ፥ ከሰዎች፥ እድል ፈንታቸው በሕይወታቸው ከሆነች ከዚህ ዓለም ሰዎች በእጅህ አድነኝ፤ ከሰወርኸው መዝገብህ ሆዳቸውን አጠገብህ፤ ልጆቻቸው ብዙ ናቸው የተረፋቸውንም ለሕፃናቶቻቸው ያተርፋሉ። እኔ ግን በጽድቅ ፊትህን አያለሁ፤ ክብርህን ሳይ እጠግባለሁ።

 ባዘነና ልመናውን በእግዚአብሔር ፊት ባፈሰሰ ጊዜ የችግረኛ ጸሎት - መዝሙር ፻፩(፻፪)

አቤቱ፥ ጸሎቴን ስማኝ፥ ጩኸቴም ወደ አንተ ይድረስ። በመከራዬ ቀን ፊትህን ከኔ አትመልስ፤ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፤ በጠራሁህ ቀን ፈጥነህ ስማኝ። ዘመኔ እንደ ጢስ አልቃለችና፥ አጥንቶቼም እንደ መቃጠያ ተቃጥለዋልና። እህል መብላት ተረስቶኛልና ተቀሠፍሁ ልቤም እንደ ሣር ደረቀ። ከጩኸቴ ድምፅ የተነሣ አጥንቶቼ ከሥጋዬ ጋር ተጣበቁ። እንደ ምድረ በዳ እርኩም መሰልሁ፤ በፈረሰ ቤት እንዳለ እንደ ጕጕት ሆንሁ። ተጋሁ፥ በሰገነትም እንደሚኖር ብቸኛ ድንቢጥ ሆንሁ። ጠላቶቼ ሁልጊዜ ይሰድቡኛል፥ የሚያሳድዱኝም ተማማሉብኝ። አመድን እንደ እህል ቅሜአለሁና፥ መጠጤንም ከእንባዬ ጋር ቀላቅያለሁና፥ ከቍጣህና ከመዓትህም የተነሣ፤ አንሥተኸኛልና፥ ጥለኸኝማልና። ዘመኖቼ እንደ ጥላ አዘንብለዋል፤ እኔም እንደ ሣር ደርቄአለሁ። አንተ ግን፥ አቤቱ፥ ለዘላለም ትኖራለህ፥ መታሰቢያህም ለልጅ ልጅ ነው። አንተ ተነሥ ጽዮንንም ይቅር በላት፥ የምሕረትዋ ጊዜ ነውና፥ ዘመንዋም ደርሶአልና፤ ባሪያዎችህም ድንጋዮችዋን ወድደዋልና፥ ለመሬትዋም አዝነዋልና። አቤቱ፥ አሕዛብ ስምህን፥ ነገሥታትም ሁሉ ክብርህን ይፈራሉ፤ እግዚአብሔር ጽዮንን ይሠራታልና፥ በክብሩም ይገለጣልና። ወደ ችግረኞች ጸሎት ተመለከተ፥ ልመናቸውንም አልናቀም። ይህ ለሚመጣ ትውልድ ይጻፍ፥ የሚፈጠርም ሕዝብ ለእግዚአብሔር እልል ይላል፤ እግዚአብሔር ከመቅደሱ ከፍታ ሆኖ ተመልክቶአልና፥ ከሰማይ ሆኖ ምድርን አይቶአልና፤ የእስረኞችን ጩኸት ይሰማ ዘንድ፥ ሊገድሉ የተፈረደባቸውን ያድን ዘንድ፤ የእግዚአብሔርን ስም በጽዮን ምስጋናውንም በኢየሩሳሌም ይናገሩ ዘንድ፤ አሕዛብ በአንድነት በተሰበሰቡ ጊዜ መንግሥታትም ለእግዚአብሔር ይገዙ ዘንድ። በኃይሉ ጎዳና መለሰለት። የዘመኔን አነስተኛነት ንገረኝ። በዘመኔ እኵሌታ አትውሰደኝ፤ ዓመቶችህ ለልጅ ልጅ ናቸው። አቤቱ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማያትም የእጅህ ሥራ ናቸው። እነርሱ ይጠፋሉ፥ አንተ ግን ትኖራለህ፤ ሁላቸው እንደ ልብስ ያረጃሉ፥ እንደ መጐናጸፊያም ትለውጣቸዋለህ፥ ይለወጡማል፤ አንተ ግን ያው አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም። የባሪያዎችህም ልጆች ይኖራሉ፥ ዘራቸውም ለዘላለም ትጸናለች።

 የነቢዩ የዕንባቆም ጸሎት በመዝሙር - ትንቢተ ዕንባቆም ፫፡፩-፲፮

አቤቱ፥ ዝናህን ሰምቼ ፈራሁ፤ አቤቱ፥ በዓመታት መካከል ሥራህን ፈጽም፤ በዓመታት መካከል ትታወቅ፤ በመዓት ጊዜ ምሕረትን አስብ። እግዚአብሔር ከቴማን፥ ቅዱሱም ከፋራን ተራራ ይመጣል። ክብሩ ሰማያትን ከድኖአል፥ ምስጋናውም ምድርን ሞልቶአል። ፀዳሉም እንደ ብርሃን ነው፤ ጨረር ከእጁ ወጥቶአል፤ ኃይሉም በዚያ ተሰውሮአል። ቸነፈር በፊቱ ይሄዳል፥ የእሳትም ነበልባል ከእግሩ ይወጣል። ቆመ፥ ምድርንም አወካት፤ ተመለከተ፥ አሕዛብንም አናወጠ፤ የዘላለምም ተራሮች ተቀጠቀጡ፥ የዘላለምም ኮረብቶች ቀለጡ፤ መንገዱ ከዘላለም ነው። የኢትዮጵያ ድንኳኖች ሲጨነቁ አየሁ፤ የምድያም አገር መጋረጃዎች ተንቀጠቀጡ። በውኑ እግዚአብሔር በወንዞች ላይ ተቈጥቶአልን? ቍጣህ በወንዞች ላይ፥ መዓትህም በባሕር ላይ ነውን? በፈረሶችህና በማዳንህ ሰረገሎች ላይ ተቀምጠሃልና። በቃልህ እንደ ማልህ መቅሠፍትህን አወጣህ፤ ቀስትህንም ገተርህ፤ ምድርን ሰንጥቀህ ፈሳሾችን አወጣህ። ተራሮች አንተን አይተው ተጨነቁ፤ የውኃ ሞገድ አልፎአል፤ ቀላዩም ድምፁን ሰጥቶአል፥ እጁንም ወደ ላይ አንሥቶአል። ፍላጾችህ ከወጡበት ብርሃን የተነሣ፥ ከሚንቦገቦገውም ከጦርህ ፀዳል የተነሣ፥ ፀሐይና ጨረቃ በመኖሪያቸው ቆሙ። በምድር ላይ በመዓት ተራመድህ፤ አሕዛብን በቍጣ አሄድሃቸው። ሕዝብህን ለመታደግ፥ የቀባኸውንም ለማዳን ወጣህ፤ የኃጢአተኛውን ቤት ራስ ቀጠቀጥህ፤ መሠረቱን እስከ አንገቱ ድረስ ገለጥህ። የአለቆችን ራስ በገዛ በትራቸው ወጋህ፤ እኔን ይበትኑ ዘንድ እንደ ዐውሎ ነፋስ መጡ፤ ችግረኛውን በስውር ለመዋጥ ደስታቸው ነው። ፈረሶችህን በባሕር፥ በብዙ ውኆችም ላይ አስረገጥህ። እኔ ሰምቻለሁ፥ ልቤም ደነገጠብኝ፤ ከድምፁ የተነሣ ከንፈሮቼ ተንቀጠቀጡ፤ መንቀጥቀጥ ወደ አጥንቶቼ ውስጥ ገባ፤ በስፍራዬ ሆኜ ተናወጥሁ፤ በሚያስጨንቁን ሕዝብ ላይ እስኪመጣ ድረስ የመከራን ቀን ዝም ብዬ እጠብቃለሁ።

  ጸሎተ ኤርምያስ - ሰቆቃወ ኤርምያስ ፭፡፩-፳፪

አቤቱ፥ የሆነብንን አስብ፤ ተመልከት ስድባችንንም እይ። ርስታችን ለእንግዶች፥ ቤቶቻችን ለሌሎች ሆኑ። ድሀ አደጎችና አባት የሌለን ሆነናል፤ እናቶቻችን እንደ መበለቶች ሆነዋል። ውኃችንን በብር ጠጣን እንጨታችንን በዋጋ ገዛን። አሳዳጆቻችን በአንገታችን ላይ ናቸው፤ እኛ ደክመናል ዕረፍትም የለንም። ለግብጻውያንና ለአሦራውያን እንጀራ እንጠግብ ዘንድ እጅ ሰጠን። አባቶቻችን ኃጢአትን ሠሩ ዛሬም የሉም፤ እኛም በደላቸውን ተሸከምን። ባሪያዎች ሠልጥነውብናል፤ ከእጃቸው የሚታደገን የለም። ከምድረ በዳ ሰይፍ የተነሣ በሕይወታችን እንጀራችንን እናመጣለን። ከሚያቃጥል ከራብ ትኩሳት የተነሣ ቁርበታችን እንደ ምድጃ ጠቈረ። በጽዮን ሴቶችን፥ በይሁዳም ከተሞች ደናግልን አጐሰቈሉ። አለቆች በእጃቸው ተሰቀሉ፤ የሽማግሌዎች ፊት አልታፈረም። ጕልማሶች ወፍጮን ተሸከሙ፥ ልጆችም ከእንጨት በታች ተሰናከሉ። ሽማግሌዎች ከአደባባይ፥ ጕልማሶች ከበገናቸው ተሻሩ። የልባችን ደስታ ቀርቶአል፤ ዘፈናችን ወደ ልቅሶ ተለውጦአል። አክሊል ከራሳችን ወድቆአል፤ ኃጢአት ሠርተናልና ወዮልን! ስለዚህ ልባችን ታምሞአል፤ ስለዚህም ነገር ዓይናችን ፈዝዞአል፤ ስለ ጽዮን ተራራ፥ ባድማ ሆናለችና፥ ቀበሮችም ተመላልሰውባታልና። አቤቱ፥ አንተ ለዘላለም ትኖራለህ፤ ዙፋንህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ነው። ስለ ምን ለዘላለም ትረሳናለህ? ስለ ምንስ ለረጅም ዘመን ትተወናለህ? አቤቱ፥ ወደ አንተ መልሰን እኛም እንመለሳለን፤ ዘመናችንን እንደ ቀድሞ አድስ። ነገር ግን ፈጽመህ ጥለኸናል፤ እጅግ ተቈጥተኸናል።

 ሕዝቅያስ ጸሎትና የጸሎቱ መልስ - ኢሳ. ፴፰፡፩-፳

ዚያም ወራት ሕዝቅያስ ለሞት እስኪደርስ ታመመ። ነቢዩም የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ወደ እርሱ መጥቶ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ትሞታለህ እንጂ በሕይወት አትኖርምና ቤትህን አስተካክል አለው። ሕዝቅያስም ፊቱን ወደ ግድግዳው መልሶ እንዲህ ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። አቤቱ፥ በፊትህ በእውነትና በፍጹም ልብ እንደ ሄድሁ ደስ የሚያሰኝህንም እንዳደረግሁ ታስብ ዘንድ እለምንሃለሁ። ሕዝቅያስም እጅግ አድርጎ አለቀሰ። የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል መጣ። ሂድ፥ ሕዝቅያስን እንዲህ በለው። የአባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጸሎትህን ሰምቻለሁ፥ እንባህንም አይቻለሁ፤ እነሆ፥ በዕድሜህ ላይ አሥራ አምስት ዓመት አጨምራለሁ። አንተንና ይህችንም ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ እታደጋለሁ፥ ይህችንም ከተማ እጋርዳታለሁ። እግዚአብሔርም የተገረውን ነገር እንዲፈጽመው ከእግዚአብሔር ዘንድ ምልክቱ ይህ ይሆንልሃል። እነሆ፥ በአካዝ የጥላ ስፍረ ሰዓት ላይ ከፀሐይ ጋር የወረደውን በደረጃዎች ያለውን ጥላ አሥር ደረጃ ወደ ኋላ እንዲመለስ አደርጋለሁ። ፀሐይም በጥላ ስፍረ ሰዓት ላይ የወረደበት አሥር ደረጃ ወደ ኋላ ተመለሰ። የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ታምሞ ከደዌው በተፈወሰ ጊዜ የጻፈው ጽሕፈት ይህ ነው። እኔ በሕይወት ዘመኔ መካከል ወደ ሲኦል በሮች እገባለሁ፤ የቀረው ዘመኔ ጐደለብኝ አልሁ። ደግሞም። በሕያዋን ምድር እግዚአብሔርን አላይም፤ በዓለምም ከሚኖሩ ጋር ሰውን እንግዲህ አልመለከትም አልሁ። ማደሪያዬ ተነቀለች፥ እንደ እረኛ ድንኳንም ከእኔ ዘንድ ተወገደች፤ ሕይወቴንም እንደ ሸማኔ ጠቀለልሁ፥ እርሱም ከመጠቅለያው ይቈርጠኛል፤ ከማለዳም ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ታጠፋኛለህ። እስኪነጋ ድረስ ቈይቼ ነበር፤ እርሱ እንደ አንበሳ አጥንቴን ሁሉ ሰበረ፤ ከማለዳ ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ታጠፋኛለህ። እንደ ጨረባና እንደ ሽመላ ተንጫጫሁ፥ እንደ ርግብም አጕረመረምሁ፤ ዓይኖቼ ወደ ላይ ከማየት ደከሙ። ጌታ ሆይ፥ ተጨንቄአለሁና መከታ ሁነኝ። ምን እላለሁ? እርሱ ተናግሮኛል፥ እርሱ ራሱም ይህን አድርጎአል፤ በዘመኔ ሁሉ ስለ ነፍሴ ምሬት ቀስ ብዬ እሄዳለሁ። ጌታ ሆይ፥ በዚህ ነገር ሰዎች በሕይወት ይኖራሉ፥ በዚህም ሁሉ የመንፈሴ ሕይወት ነው፤ አንተም ፈወስኸኝ ወደ ሕይወትም መለስኸኝ። እነሆ፥ ታላቅ ምሬት ለደኅንነቴ ሆነ፤ አንተም ነፍሴን ከጥፋት ጕድጓድ አዳንሃት፥ ኃጢአቴንም ሁሉ ወደ ኋላህ ጣልህ። ሲኦል አያመሰግንህምና፥ ሞትም አያከብርህምና፤ ወደ ጕድጓዱ የሚወርዱ እውነትህን ተስፋ አያደርጉም። እኔ ዛሬ አንደማደርግ ሕያዋን እነርሱ ያመሰግኑሃል፤ አባት ለልጆች እውነትህን ያስታውቃል። እግዚአብሔር ያድነኛል፤ ስለዚህ በዕድሜያችን ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት ቅኔዎችን አውታር ባለው ዕቃ እንዘምራለን።

 ጸሎተ ሐና - ፩ መጽ. ሳሙ. ፪፤፲

ሐናም ስትጸልይ እንዲህ አለች። ልቤ በእግዚአብሔር ጸና፥ ቀንዴ በእግዚአብሔር ከፍ ከፍ አለ፤ አፌ በጠላቶቼ ላይ ተከፈተ፤ በማዳንህ ደስ ብሎኛል። እንደ እግዚአብሔር ቅዱስ የለምና፥ እንደ አምላካችንም ጻድቅ የለምና፤ ከአንተ በቀር ቅዱስ የለም። አትታበዩ፥ በኩራትም አትናገሩ፤ እግዚአብሔር አዋቂ ነውና፥ እግዚአብሔርም ሥራውን የሚመዝን ነውና፥ ከአፋችሁ የኵራት ነገር አይውጣ። የኃያላንን ቀስት ሰብሮአል፥ ደካሞችንም በኃይል ታጥቀዋል። ጠግበው የነበሩ እንጀራ አጡ፤ ተርበው የነበሩ ከራብ ዐርፈዋል፤ መካኒቱ ሰባት ወልዳለችና፥ ብዙም የወለደችው ደክማለች። እግዚአብሔር ይገድላል ያድናልም፤ ወደ ሲኦል ያወርዳል፥ ያወጣል። እግዚአብሔር ድሀ ያደርጋል፥ ባለጠጋም ያደርጋል፤ ያዋርዳል፥ ደግሞም ከፍ ከፍ ያደርጋል። ከሕዝቡ መኳንንት ጋር ያስቀምጣቸው ዘንድ፥ የክብርንም ዙፋን ያወርሳቸው ዘንድ፥ ችግረኛውን ከመሬት ያስነሣል፥ ምስኪኑንም ከጉድፍ ያስነሣል፤ የምድር መሠረቶች የእግዚአብሔር ናቸውና፥ በእነርሱ ላይም ዓለምን አደረገ። እርሱ የቅዱሳኑን እግር ይጠብቃል ኃጥኣን ግን ዝም ብለው በጨለማ ይቀመጣሉ፤ ሰው በኃይሉ አይበረታምና። ከእግዚአብሔር ጋር የሚጣሉ ይደቅቃሉ፤ በሰማይም ያንጐደጕድባቸዋል፤ እግዚአብሔር እስከ ምድር ዳርቻ ይፈርዳል፤ ለንጉሡም ኃይል ይሰጣል፤ የመሲሑንም ቀንድ ከፍ ከፍ ያደርጋል።

ጸሎተ ሙሴ - መዝ. ፺፡፩-፳-፲፯

የእግዚአብሔር ሰው የሙሴ ጸሎት። አቤቱ፥ አንተ ለትውልድ ሁሉ መጠጊያ ሆንህልን። ተራሮች ሳይወለዱ፥ ምድርም ዓለምም ሳይሠሩ፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ አንተ ነህ። ሰውን ወደ ኅሳር አትመልስም፤ የሰው ልጆች ሆይ፥ ተመለሱ ትላለህ፤ ሺህ ዓመት በፊትህ እንዳለፈች እንደ ትናንት ቀን፥ እንደ ሌሊትም ትጋት ነውና። ዘመኖች የተናቁ ይሆናሉ፥ በማለዳም እንደ ሣር ያልፋል። ማልዶ ያብባል ያልፋልም፥ በሠርክም ጠውልጎና ደርቆ ይወድቃል። እኛ በቍጣህ አልቀናልና፥ በመዓትህም ደንግጠናልና። የተሰወረውን ኃጢአታችንን በፊትህ ብርሃን፥ በደላችንንም በፊትህ አስቀመጥህ። ዘመናችን ሁሉ አልፎአልና፥ እኛም በመዓትህ አልቀናልና፤ ዘመኖቻችንም እንደ ሸረሪት ድር ይሆናሉ። የዘመኖቻችንም ዕድሜ ሰባ ዓመት፥ ቢበረታም ሰማንያ ዓመት ነው፤ ቢበዛ ግን ድካምና መከራ ነው፤ ከእኛ ቶሎ ያልፋልና፥ እኛም እንገሠጻለንና። የቍጣህን ጽናት ማን ያውቃል? ከቍጣህ ግርማ የተነሣ አለቁ። በልብ ጥበብን እንድንማር፥ ቀኝህን እንዲህ አስታውቀን። አቤቱ፥ ተመለስ፥ እስከ መቼስ ነው? ስለ ባሪያዎችህም ተምዋገት። በማለዳ ምሕረትህን እንጠግባለን፤ በዘመናችን ሁሉ ደስ ይለናል ሐሤትም እናደርጋለን። መከራ ባሳየኸን ዘመን ፈንታ፥ ክፉም ባየንባቸው ዘመኖች ፋንታ ደስ ይለናል። ባሪያዎችህንና ሥራህን እይ፥ ልጆቻቸውንም ምራ። የአምላካችን እግዚአብሔር ብርሃን በላያችን ይሁን። የእጆቻችንንም ሥራ በላያችን አቅና።

 የእግዚአብሔር ሰው የሙሴ ጸሎትና የእግዚአብሔር መልስ - ዘጸ. ፴፪፡፲፩-፲፮

ሙሴም በእግዚአብሔር በአምላኩ ፊት ጸለየ፥ አለም። አቤቱ፥ ቍጣህ በታላቅ ኃይልና በጽኑ እጅ ከግብፅ ምድር ባወጣኸው በሕዝብህ ላይ ስለ ምን ተቃጠለ? ግብፃውያንስ። በተራራ መካከል ሊገድላቸው፥ ከምድርም ፊት ሊያጠፋቸው ለክፋት አወጣቸው ብለው ስለ ምን ይናገራሉ? ከመዓትህ ተመለስ፥ ለሕዝብህም በክፋታቸው ላይ ራራ። ዘራችሁን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ፥ ይህችንም የተናገርኋትን ምድር ሁሉ ለዘራችሁ እሰጣታለሁ፥ ለዘላለምም ይወርሱአታል ብለህ በራስህ የማልህላቸውን ባሪያዎችህን አብርሃምንና ይስሐቅን እስራኤልንም አስብ። እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ ሊያደርግ ስላሰበው ክፋት ራራ። ሙሴም ተመለሰ፥ ሁለቱንም የምስክር ጽላቶች በእጁ ይዞ ከተራራው ወረደ፤ ጽላቶቹም በዚህና በዚያ በሁለት ወገን ተጽፎባቸው ነበር። ጽላቶቹም የእግዚአብሔር ሥራ ነበሩ፤ ጽሕፈቱም በጽላቶች ላይ የተቀረጸባቸው የእግዚአብሔር ጽሕፈት ነበረ።

 ጸሎተ ነህምያ - ነህምያ ፩-፭-፲፩

አቤቱ የሰማይ አምላክ ሆይ፥ ለሚወድዱህና ትእዛዝህን ለሚያደርጉ ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ፥ ታላቅና የተፈራህ አምላክ ሆይ፥ እኔ ባሪያህ ዛሬ በፊትህ ስለ ባሪያዎችህ ስለ እስራኤል ልጆች ሌሊትና ቀን የምጸልየውን ጸሎት ትሰማ ዘንድ ጆሮህ ያድምጥ፥ ዓይኖችህም ይከፈቱ፤ በአንተ ላይም ያደረግነውን የእስራኤልን ልጆች ኃጢአት እናዘዝልሃለሁ፤ እኔና የአባቴም ቤት በድለናል። እኛም በአንተ ላይ እጅግ ክፉ ሠርተናል፤ ለባሪያህም ለሙሴ ያዘዝኸውን ትእዛዝና ሥርዓት ሕግም አልጠበቅንም። አሁንም ብትተላለፉ በአሕዛብ መካከል እበትናችኋለሁ፤ ወደ እኔ ብትመለሱ ግን ትእዛዜንም ብትጠብቁ ብታደርጓትም፥ ከእናንተ ሰዎች እስከ ሰማይ ዳርቻ ድረስ ምንም ቢበተኑ ከዚያ እሰበስባቸዋለሁ፥ ስሜም ይኖርበት ዘንድ ወደ መረጥሁት ስፍራ አመጣቸዋለሁ ብለህ ለባሪያህ ለሙሴ ያዘዝኸውን ቃል እባክህ አስብ። እነዚህም በታላቅ ኃይልህና በብርቱ እጅህ የተቤዠሃቸው ባሪያዎችህና ሕዝብህ ናቸው። ጌታ ሆይ፥ ጆሮህ የባሪያህን ጸሎት፥ ስምህንም ይፈሩ ዘንድ የሚወድዱትን፥ የባሪያዎችህን ጸሎት ያድምጥ፤ ዛሬም ለባሪያህ አከናውንለት፥ በዚህም ሰው ፊት ምሕረትን ስጠው። እኔም ለንጉሡ ጠጅ አሳላፊው ነበርሁ።

 የጠቢቡ ሰሎሞን ጸሎት - ፩ መጽ. ነገሥት ፰፡፳፪-፶፬

የእስራኤልም ጉባኤ ሁሉ እያዩ ሰሎሞን በእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት ቆሞ እጆቹን ወደ ሰማይ ዘረጋ። እንዲህም አለ። የእስራኤል አምላክ አቤቱ፥ በላይ በሰማይ በታችም በምድር አንተን የሚመስል አምላክ የለም፤ በፍጹም ልባቸው በፊትህ ለሚሄዱ ባሪያዎችህ ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ፥ ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸውን ተስፋ የጠበቅህ፤ በአፍህ ተናገርህ፥ እንደ ዛሬው ቀንም በእጅህ ፈጸምኸው። አሁንም የእስራኤል አምላክ አቤቱ። አንተ በፊቴ እንደ ሄድህ ልጆችህ መንገዳቸውን ቢጠብቁ፥ በእስራኤል ዙፋን የሚቀመጥ ሰው በፊቴ አታጣም ብለህ ተስፋ የሰጠኸውን ለአባቴ ለዳዊት ጠብቅ። አሁንም፥ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት የተናገርኸው ቃል፥ እባክህ፥ ይጽና። በውኑ እግዚአብሔር ከሰው ጋር በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ፥ ሰማይ ከሰማያትም በላይ ያለው ሰማይ ይይዝህ ዘንድ አይችልም፤ ይልቁንስ እኔ የሠራሁት ቤት እንዴት ያንስ! ነገር ግን፥ አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ ወደ ባሪያህ ጸሎትና ልመና ተመልከት፥ ዛሬም ባሪያህ በፊትህ የሚጸልየውን ጸሎትና ጥሪውን ስማ፤ ባሪያህ ወደዚህ ስፍራ የሚጸልየውን ጸሎት ትሰማ ዘንድ። በዚያ ስሜ ይሆናል ወዳልኸው ስፍራ ወደዚህ ቤት ዓይኖችህ ሌሊትና ቀን የተገለጡ ይሁኑ። ባሪያህና ሕዝብህ እስራኤል ወደዚህ ስፍራ የሚጸልዩትን ልመና ስማ፤ በማደሪያህ በሰማይ ስማ፤ ሰምተህም ይቅር በል። ሰው ባልንጀራውን ቢበድል፥ በላዩም መሐላ ቢጫን፥ እርሱም መጥቶ በዚህ ቤት በመሠዊያህ ፊት ቢምል፥ በሰማይ ስማ አድርግም፤ በባሪያዎችህም ላይ ዳኛ ሁን፤ በበደለኛውም ላይ ፍረድ፥ መንገዱንም በራሱ ላይ መልስበት፤ ንጹሑን አጽድቀው፥ እንደ ጽድቁም ክፈለው። ሕዝብህ እስራኤል አንተን ስለ በደሉ በጠላቶቻቸው ፊት ድል በተመቱ ጊዜ፥ ወደ አንተ ቢመለሱ፥ ስምህንም ቢያከብሩ፥ በዚህም ቤት ቢጸልዩና ቢለምኑህ፥ አንተ በሰማይ ስማ፤ የሕዝብህንም የእስራኤልን ኃጢአት ይቅር በል፥ ለአባቶቻቸውም ወደ ሰጠሃት ምድር መልሳቸው። አንተን ስለ በደሉ ሰማይ በተዘጋ ጊዜ ዝናብም ባልዘነበ ጊዜ፥ ወደዚህ ስፍራ ቢጸልዩ፥ ስምህንም ቢያከብሩ፥ ባስጨነቅሃቸውም ጊዜ ከኃጢአታቸው ቢመለሱ፥ አንተ በሰማይ ስማ፤ የሚሄዱበትንም መልካም መንገድ በማሳየት የባሪያዎችህንና የሕዝብህን የእስራኤልን ኃጢአት ይቅር በል፤ ለሕዝብህም ርስት አድርገህ ለሰጠሃት ምድር ዝናብ ስጥ። በምድር ላይ ራብ፥ ወይም ቸነፈር፥ ወይም ዋግ፥ ወይም አረማሞ፥ ወይም አንበጣ፥ ወይም ኩብኩባ ቢሆን፥ የሕዝብህም ጠላት የአገሩን ቀበሌዎች ከብቦ ቢያስጨንቃቸው፥ መቅሠፍትና ደዌ ሁሉ ቢሆን፥ ማናቸውም ሰው የልቡን ሕመም አውቆ ጸሎትና ልመና ቢጸልይ፥ እጆቹንም ወደዚህ ቤት ቢዘረጋ፥ ለአባቶቻችን በሰጠሃት ምድር ላይ በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ ይፈሩህ ዘንድ በማደሪያህ በሰማይ ስማ፥ ይቅርም በል፤ አንተ ብቻ የሰውን ልጆች ሁሉ ልብ ታውቃለህና ልቡን ለምታውቀው ሰው ሁሉ እንደ መንገዱ ሁሉ መጠን ክፈለውና ስጠው። ከሕዝብህም ከእስራኤል ወገን ያልሆነ እንግዳ ታላቁን ስምህን፥ ብርቱይቱንም እጅህን፥ የተዘረጋውንም ክንድህን ሰምቶ ስለ ስምህ ከሩቅ አገር በመጣ ጊዜ፥ መጥቶም ወደዚህ ቤት በጸለየ ጊዜ፥ አንተ በማደሪያህ በሰማይ ስማ፤ የምድርም አሕዛብ ሁሉ ስምህን ያውቁ ዘንድ እንደ ሕዝብህም እንደ እስራኤል ይፈሩህ ዘንድ፥ በዚህም በሠራሁት ቤት ስምህ እንደተጠራ ያውቁ ዘንድ፥ እንግዳው የሚለምንህን ሁሉ አድርግ። ሕዝብህም ጠላቶቻቸውን ለመውጋት አንተ በምትልካቸው መንገድ ቢወጡ፥ አንተም ወደ መረጥሃት ከተማ እኔም ለስምህ ወደ ሠራሁት ቤት ለእግዚአብሔር ቢጸልዩ፥ ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በሰማይ ስማ፥ ፍርድንም አድርግላቸው። የማይበድልም ሰው የለምና አንተን ቢበድሉ፥ ተቈጥተህም ለጠላቶቻቸው አሳልፈህ ብትሰጣቸው ሩቅ ወይም ቅርብ ወደ ሆነ ወደ ጠላቶች አገር ቢማረኩም፥ በተማረኩበትም አገር ሆነው በልባቸው ንስሐ ቢገቡ፥ በማራኪዎቹም አገር ሳሉ ተመልሰው። ኃጢአት ሠርተናል፥ በድለንማል፥ ክፉንም አድርገናል ብለው ቢለምኑህ፥ በማረኩአቸው በጠላቶቻቸው አገር ሳሉ በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው ወደ አንተ ቢመለሱ፥ ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠሃት ወደ ምድራቸው ወደ መረጥሃትም ከተማ ለስምህም ወደ ሠራሁት ቤት ቢጸልዩ፥ ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በማደሪያህ በሰማይ ስማ፥ ፍርድንም አድርግላቸው፥ አንተንም የበደሉህን ሕዝብህን፥ በአንተም ላይ ያደረጉትን በደላቸውን ሁሉ ይቅር በል፤ ይራሩላቸውም ዘንድ በማረኩአቸው ፊት ምሕረት ስጣቸው፤ ከግብፅ ምድር ከብረት እቶን ውስጥ ያወጣሃቸው ሕዝብህና ርስትህ ናቸውና። በጠሩህ ጊዜ ሁሉ ትሰማቸው ዘንድ ለባሪያህና ለሕዝብህ ለእስራኤል ልመና ዓይኖችህ የተገለጡ ይሁኑ። ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ አባቶቻችንን ከግብጽ ባወጣህ ጊዜ በባሪያህ በሙሴ እጅ እንደ ተናገርህ ርስት ይሆኑህ ዘንድ ከምድር አሕዛብ ሁሉ ለይተሃቸዋልና። ሰሎሞንም ይህችን ጸሎትና ልመና ሁሉ ለእግዚአብሔር ጸልዮ በፈጸመ ጊዜ፥ በጕልበቱ ተንበርክኮ እጁንም ወደ ሰማይ ዘርግቶ ነበርና ከእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት ተነሣ።

የነቢዩ ዮናስ ጸሎት - ትንቢተ ዮናስ ምዕራፍ ፪፤፫-፲

በመከራዬ ሳለሁ ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ፥ እርሱም ሰማኝ፤ በሲኦልም ሆድ ውስጥ ሆኜ ጮኽሁ፥ ቃሌንም አዳመጥህ። ወደ ጥልቁ ወደ ባሕሩ ውስጥ ጣልኸኝ፥ ፈሳሾችም በዙሪያዬ ነበሩ፤ ማዕበልህና ሞገድህ ሁሉ በላዬ አለፉ። እኔም፥ ከዓይንህ ፊት ተጣልሁ፤ ነገር ግን ወደ ቅዱስ መቅደስህ ደግሞ እመለከታለሁ አልሁ። ውŠችም እስከ ነፍሴ ድረስ ከበቡኝ፤ ጥልቁ ባሕር በዙሪያዬ ነበረ፤ የባሕሩ ሣር በራሴ ተጠምጥሞ ነበር። ወደ ተራሮች መሠረት ወረድሁ፤ በምድርና በመወርወሪያዎችዋ ለዘላለም ተዘጋሁ፤ አንተ ግን፥ አቤቱ አምላኬ፥ ሕይወቴን ከጕድጓዱ አወጣህ። ነፍሴ በዛለችብኝ ጊዜ እግዚአብሔርን አሰብሁት፤ ጸሎቴም ወደ አንተ ወደ ቅዱስ መቅደስህ ገባች። ከንቱነትንና ሐሰትን የሚጠብቁ ምሕረታቸውን ትተዋል። እኔ ግን በምስጋና ቃል እሠዋልሃለሁ፤ የተሳልሁትንም እከፍላለሁ። ደኅንነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።